ለመሆኑ የልጆቻችን ሕይወት በየትኛው ሁኔታና እውነታ ውስጥ ይገኛል?
ሕጻናት የሚያንፀባርቁት ባሕርይ በአብዛኛው በቤት ውስጥ ባለው ሕይወት ተጽዕኖ ሥር የወደቁ ናቸው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ፣ ልብስ፣ ጥበቃና እንክብካቤ ያገኛሉ? በቂ እንቅልፍስ ይተኛሉ? እነዚህንና መሰል አካባቢያዊ ሁኔታዎች በሕጻናት ባሕርያት ይንፀባረቃሉ፡፡ የያንዳንዱ ሕጻን ባሕርይ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር የተገናኘና የተዛመደ ነው፡፡ ሕጻኑ የእድሜውን ይተውናል/ያከናውናል/ይተገብራል ነው፡፡ ለሕጻናት ርኅሩኅ፤ ደግና ቸር እንሁንላቸው፡፡ በአክብሮትና ጨዋነት እንከባከባቸው፡፡ እያንዳንዱ ሕጻን የመከበርና የተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ለጤናማ እድገቱ በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በምንም ምክንያት በየአጋጣሚው ሁሉ ማፌዝ፣ ማላገጥ ወይም ሕጻኑን ማሳነስ፣ ማንኳሰስና በሕጻኑ ላይ አላስፈላጊ ድርጊቶችን መፈፀም ክፋት የተሞላበት ተግባር ነው፡፡ በሕጻናት መካከል አድሏዊ ከመሆን እንቆጠብ፡፡ ሁሌጊዜ ግልፅና ሚዛናዊ መሆናችንን እናሳያቸው፡፡ ሕጻናት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ግልፅ፤ ቅን፣ ታማኝ፣ ለእድሜያቸውና ለእድገት ደረጃቸው ተስማሚ መልሶች መመለስ ከመምህራንና ወላጆች የሚጠበቅ የዘወተር ተግባር ነው፡፡ ቃል ከገባ ማክበር አስፈላጊ ነው። በወቅቱ መፈፀም የማንችል ከሆነ ከመጀመሪያው ቃል ባንገባ ይመረጣል፡፡ ሕጻናት በቀላሉ የሚያምኑና የሚታለሉ ናቸው፡፡ ሕጻናት በስርዓት ሲያዙ፣ ሞቅ፣ ደመቅ ያለ አቀባበልና እንክብካቤ ሲደረግላቸው መልካም ባሕሪያትን በመቅሰም ተመሳሳይ ጠባያትን ያንፀባርቃሉ፡፡ ለሕጻናት ድጋፍና እንክብካቤ የምናደርግ ሁሉ በሕጻናት ሰብዕና ላይ የበኩላችንን አሻራ የምናሳርፍና ዕጣ ፋንታቸውን ወሳኝ አንድ ኃይል መሆናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡
መልካም፣ መልካሙን ለሕፃናት!!
ሣህሉ ባዬ ዓለሙ
Comments