call us now

251 1 911 23 08 57 / 60 76 06

Living for others

ነገሩቅነውን?

የነገውን ሰው ማነጽ

ይድረስ ለአፀደ-ሕፃናት መምህራን!

ባሳለፍነው ዓመት ሕፃናት ጤናማ የሆነ አካል፣ አእምሯሮ፣ ስሜትና ማህበረ-ስነልቦና ተላብሰው እንዲያድጉ በማስቻል አስፈላጊውን ጥረት ላደረጋችሁ የአፀደ-ሕፃናት መምህራን እንኳን ለ2010 አዲስ ዓመትና አዲሱ የትምህርት ዘመን በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ በሕፃናት አስተዳደግ ሂደት ውሰጥ የመምህራን ሚናን በተመለከተ አንድ፤ ሁለት…ነጥቦችን ለማንሳት ወደ ዛሬዋ መልዕክቴ እሸጋገራለሁ፡፡

     የመጀመሪያው መሰረታዊ ነጥብ የመምህር፤ ወላጅና ልጅ ግንኙነት ረብ-የለሽ ከሆነ የሕፃኑ አእምሮአዊ፣ አካላዊ፣ ስሜታዊና ማኅበረ-ስነልቦናዊ ዕድገቶች በእጅጉ የሚደናቅፉ መሆናቸውን መረዳት ነው፡፡ በልክ የተቀናጀና ትርጉም ያለው የመማር-ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር መምህራን የወላጆችን ፍላጎትና በወላጆችና ልጆች መካከል ያለውን ግንኙነት ማወቅ ይኖርብናል፡፡ የሰውን ችግር እንደራስ ችግር የማዳመጥና ግልጽነት የሰፈነበት የቡድን ውይይት ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ውይይት መምህራን የማይቃወሙ መሪዎች (Passive Leaders) በመሆን ወላጆች ደግሞ ስለ ልጆች አስተዳደግ ያሏቸውን ልምዶች በውይይቱ ላይ ንቁ ተሳታፊ (Active Participants) በመሆን ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ለምሳሌ ውይይቱ የሚያጠነጥንባቸው ጉዳዮች ወላጆች ስለ ጥሩ ልጅምንነት ባላቸው አስተያየት ወይም አንድ ሕፃን ጥሩ ልጅእንዲሆን የወላጆች ሚና ምን መሆን እንዳለበትና ወላጆች ራሳቸው በወላጆቻቸው እንዴት ጥሩ ልጆችሆነው እንዲያደጉ እንደተደረገ ባላቸው ተሞክሮ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ተመራማሪ ዶ/ር ኔኻማ መምህራን ከወላጆች የሚማሩ ከሆነ ልጆችን በተሻለ ሁኔታ ሊያስተምሩ ይችላሉ ብለው ያምናሉ፡፡ በሦስት፣ አራት ወይም አምስት ዓመት ዕድሜያቸው ወደ አፀደ-ሕፃናት የመጡ ሕፃናት በቤት ውስጥ ባገኟቸው ልምዶች ሳቢያ የተሻለ አእምሮአዊ ቅርፅ ሊኖራቸው ይችላል፡፡

     ሁለተኛው ነጥብ ወላጆች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አስፈላጊውን መልስ በወቅቱ መስጠት ወይም ማስረዳት የእኛ የመምህራን ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ወላጆች ከአፀደ-ሕፃናት ግቢ ውጪ እንዲሆኑ አናስገድዳቸው፡፡ የሕፃናትን የት/ቤት ውሎ ለወላጆች ማካፈል የተግባራችን አንዱ አካል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የምናስተምራቸው ሕፃናት የእነርሱ ልጆች ስለሆኑ በሕይወታቸው ከልጆቻቸው በላይ የሚወዱት ነገር ያለመኖሩን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ልጆችም ከወላጆቻቸው በላይ ማንንም አይወዱም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው በሚማሩባቸው ት/ቤቶች እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ አፀደ-ሕፃናቱንም እንዲጎበኙልንና ፈቃደኛ ከሆኑም ደግሞ ድጋፍ እንዲያደርጉልን ለማበረታታት ወላጆችን በእንኳን ደህና መጡ አቀባበል ምቾት መስጠት ቀዳሚ ተግባራችን መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ የዋላጆች ስሜት በቦጎ ምልኩ መቀየር የልጆቻቸውን ስሜት ይቀይራል፡፡ ሕፃናት ወደ አፀደ-ሕፃናት በመሄዳቸው ወላጆቻቸው የሚደሰቱ መሆናቸውን ካስተዋሉ ሁሌም በአፀደ-ሕፃናቱ ውስጥ ለመገኘት ፈቃደኞች ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ከመምህራንና ወላጆች ጤናማ ግንኙነት ይበልጥ ተጠቃሚዎቹ ሕፃናት መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ወላጅ መሆን ቀላል ነገር ስላልሆነ ለወላጆች ስሜት ተገቢውን ክብርና ድጋፍ እንስጥ፡፡ ወላጆች የግል ጉዳያቸውን ለእኛ ለማካፈል ፍላጎት ካሳዩና ግልፅ ከሆኑ በአክብሮትና በጥሞና እናዳምጣቸው፡፡ ከተቻለም አረጋጊና አዝናኝ እንሁንላቸው፡፡ ያገኘነው መረጃ በየትኛውም ሁኔታ እንዳይባክን ሚስጥር ጠባቂ መሆን ይኖርብናል፡፡ እኛ መምህራን ክቡር ባለሙያዎች ስለሆንን የያዝነውን መረጃ የሙያ አጋር ካልሆነ ሰው ጋር መወያየት አይኖርብንም፡፡

     ሦስተኛው ነጥብ ልጆች በአፀደ-ሕፃናት ውሏቸው የተማሯቸውንና ያከናወኗቸውን ወላጆች እንዲመለከቷቸው ከተቻለም እንዲተገብሯቸው ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ እነዚህ መድረኮች ወላጆች የልጆቻቸውን ሙከራ እንዲሁም ምን ተምረው ምን እንዳወቁ በመፈተሽ ግንዛቤ እንዲያገኙ ይረዷቸዋል፡፡ ዘወትር ለሕፃናት የምናደርገው የሞቀ አቀባበልና አሸኛኘት፣ ለስራችን የምናደርገው ጥንቃቄና የምንሰጠው ትኩረት መገለጫ መሆኑን ተረድተን ወላጆች እንዲረዱን እንጣር፡፡

     አራተኛው ነጥብ ወላጆች ለአፀደ-ሕፃናት ጠቃሚ ሀብት መሆናቸውን መረዳት ነው፡፡ አንዳንድ ወላጆች በክፍል ውስጥ ለሕፃናት ታሪክ በመተረክ፣ ተረት በማውጋት፣ ዘፈኖችን በመዝፈን፤ ዜማዎችን በማዜም ወይም በመዘመር ነፃ አገልግሎት መስጠት ያስደስታቸው ይሆናል፡፡ አንዳንድ ወላጆች የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወትና ያልተለመዱ፣ ብርቅዬና ተወዳጅ እንስሳትን በማስተዋወቅ የትምህርት መርሃ-ግብሩን ማጎልበት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ወላጆች ምግብ ማዘጋጀት ወይም ማብሰል ይፈልጉ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ወላጆች የስብሰባ ዕቅድ ማዘጋጀት ይመርጡ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ግልፅና ወዳጃዊ የሆኑ ወላጆች ደግሞ ስለ ልምዳቸውና ግላዊ ሕይዎታቸው ሊያካፍሉን ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ለወላጆች የተዘጋጀው ፕሮግራም ምንም ይሁን ምን ለባህል፣ ለዘር፣ ለጎሳ፣ ለብሔር፤ ለብሔረሰብና ለሃይማኖታዊ ልዩነቶች አክብሮት መስጠት ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆነ ትኩረት እንስጥ፡፡ የወላጆች ምርጫ ምንም ይሁን ምን ምርጫቸው ይከበር፡፡ ይህንንም ዕድል ስንጠቀም ባለን ዕውቀት ላይ ተጨማሪ ዕውቀት አገኘን ማለት ነው፡፡

     አምስተኛውና አንኳር ነጥብ የቀዳማይ ልጅነት የዕደገት ሂደት መገለጫዎችን ተረድቶ እነሱን ማጎልበት ነው፡፡ ይህ የዕድገት ሂደት የሕፃናት አእምሮ የሚለወጥበትና የሚለጠጥበት፤ ሕፃናት ከአካባቢያቸው ጋር በሚያደርጉት መስተጋብርና በሚያገኟቸው ማነቃቂያዎች የአእምሮ ሴሎቻቸው እርስ በርሳቸው የሚገናኙበትና የሚናበቡበት፤ የመማር ፍላጎታቸው መሰረት የሚጣልበት፤ ክሂሎት፤ ጥበብ፤ ዘዴ፤ ችሎታቸውና የማህበራዊ ግንኙነታቸው አድማስ የሚሰፋበት……ወቅት መሆኑን ተረድተን የሕፃናትን አእምሮ ለማበልፀግ መጣር ይጠበቅብናል፡፡ ስለሆነም ወደ ግባችን ለማምራት ስራችንን በአትኩሮት ማከናወን (Focusing)፣ ጤናማ የባህርይ ለውጥ የሚያስከትል የዕውቀት ሽግግር ማድረግ (Mediation of Meaning)፣ ዕውቀትን ማሻሻልና ማስፋፋት (Transcendence)፣ ሕፃናት የብቃት ስሜት እንዲያዳብሩ ማስቻል (Mediation of Competence)፣ ባሕርይን የመከታተልና የመቆጣጠር ልምድን በማዳበር (Regulation of Behavior) የሕፃናትን ሰብዕና መቅረፅ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የመሰረታዊ ዕውቀት ማሸጋገሪያ ዘዴዎችን ማለትም መዝሙሮችን፤ ዘፈኖችን፤ የሚያስደስቱና የሚያዝናኑ ቀልዶችን፤ የተለያዩ ጨዋታዎችን፤ ሥዕሎችን፤ ትምህርታዊ ንግግሮችን፤ የፈጠራ ሥራዋችን፤ አስተውሎት ወይም ምልከታዎችን፤ ትርጉሞችና ማብራሪያዎችን፤ ጥያቄና መልሶችን፤ ዘገባዎችን፤ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን፤ ማበረታቻዎችን፤ ጭፈራና ዳንሶችን፤ አዳዲስ ግኝቶችን፤ የዕንግዳ ግብዣን፤ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ወይም ልምምዶችን፤ ትዕግስትን፤ ምክንያታዊነትን……ወዘተ በቅድመ መደበኛ የመማር-ማስተማርና ሂደት ውስጥ የማይተካ አስተዋጽዖ ያላቸው መሆኑን ተረድተን መተግበር ይጠበቅብናል፡፡ እያንዳንዱ የሕፃኑ የዕድገት ስኬት ሕፃኑን ለቀጣይ የዕድገት ሂደት ያዘጋጀዋል፡፡ ምንም እንኳን በሕፃናት መካከል ግላዊ የሆኑ ልዩነቶች ቢስተዋሉም አጠቃላዩ የዕድገት ሂደት ጉዞ ግን ለሁሉም ተመሳሳይነት አለው፡፡ የሕፃናት ጤናማና የተስተካከለ እድገት ወደላይ የማደግ አቅጣጫን ያመለክታል፡፡ በመማር-ማስተማር ሂደት ውስጥ ለሕፃናት ጤናማ ዕድገት አስተዋጽዖ ከሚያበረክቱ ስነልቦናዊና ፔዳጎጅካዊ አቀራረቦች ውስጥ የሚከተሉትን የዕድገት ሂደቶች ማስተዋል ጠቃሚ ነው፡፡

 1. በመማሪያ ክፍላችን ውስጥ ያሉ ሕፃናት ሁሉ አሁን በደረሱበት የዕድገት ደረጃ ላይ የነበሩ አለመሆናቸውን መረዳት፡-

እነዚህ ሕፃናት በለጋነታቸው ሙሉ በሙሉ የሌሎች ጥገኞች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ራሳቸውን መርዳት ፈልገዋል፡፡ በራሳቸው ዙሪያ ስለምትሽከረከረው ትንሿ ዓለም ጥቂት ነገሮችን ማወቅ ጀምረዋል፡፡ አሁን ያች ትንሽ ዓለም እየሰፋችና እየተለጠጠች መጥታለች፡፡ ይሁን እንጂ በአፀደ-ሕፃናት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ስለራሳቸው ብቻ ስለሚያስቡና ማንኛውንም ነገር ከራሳቸው ዕይታ አንፃር ብቻ ስለሚመለከቱ የራስ ወዳድነት (Ego-Centeric) ጠባይ ያጠቃቸዋል፡፡ አንድ ሕፃን አዘውትሮ የሚያንፀባርቃቸው ቃላት ራሱን ብቻ የሚወክሉ ለምሳሌ እንደ “እኔ”“የእኔ” የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ሕፃኑ በለጋ ዕድሜው በራሱ ዙሪያ የሚገኝ ማንኛውም ነገር የእርሱ የግል ንብረት እንደሆነ ወይም የእርሱ መሆን እንደሚገባው አድርጎ ያምናል፡፡ ለምሳሌ “ይህ የእኔ ነው‹‹ይህ የእኔ ኳስ ነው››“እሷ የእኔ እናት ነች” ፣“ያን እፈልጋለሁ” የሚሉ አባባሎችን ደጋግሞ ይጠቀማል፡፡ የአፀደ-ሕፃናት ከባቢ እነዚህን ባህርያት ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡

      በአንድ ወቅት እናት፣ አባትና የቅርብ ቤተሰብ አባላትን ብቻ ያካትት የነበረው ጠባብና ውስን አካባቢ አሁን ሰፋ ወዳለ አካባቢነት ተለውጧል፡፡ የአካባቢው መለወጥ በርካታ ሌሎች ሰዎች በአካባቢው መኖራቸውን እንዲያውቅ ወይም እንዲረዳ ማረጋገጫ ሆኖለታል፡፡ ለምሳሌ መምህራን፣ ነርሶች፣ የጥበቃ ሰራተኞች፣ የፅዳት ሰራተኞች፣ አትክልተኞች…… በዙሪያው መኖራቸውን እየተረዳ ነው፡፡ ሕፃኑ አሁን ለተጨማሪ አዳዲስ ሁኔታዎች ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ከወላጆቹ ሌላ በት/ቤቱ ውስጥ ትልቅና ጎልማሳ የሆኑ መምህራንና እጅግ በርካታ አዳዲስ ፊቶች ያሏቸውን ሕፃናት ማየት ጀምሯል፡፡ የሕፃኑ ዓለም እየተቀያየረ መጓዙን ቀጥሏል፡፡ ባሕርይውም እንዲሁ፡፡ እሱም ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር እራሱን የማስማማትና የማለማመድ ፈተናን እየተጋፈጠ በመጓዝ ላይ ነው፡፡ በአዳዲስ አካባቢያዊ ሁኔታዎች በመዋጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚያስተውላቸው ነገሮችና ክስተቶች ጋር እራሱን እያለማመደ ዕድገቱን ቀጥሏል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የሚከናወነው በተከታታይ በሚተገበር ሙከራና ልምምድ ነው፡፡ ካተጨባጭ ተሞክሮ፣ ልምድና ዕውቀት እንዴት ሊገኝ ይችላል? ሕፃኑ ይጥራል፤ በአካባቢው የሚያገኘውን ማንኛውንም ነገር ይሞክራል፡፡ ሁሉንም ነገሮች ለመመርመር ይጣደፋል፡፡ አዳዲስ ስኬቶችና ትንንሽ ዕውቀቶችን ወደ እራሱ ስብስብ ለማካተት ይጓጓል፡፡ ያገኛቸውን ነገሮች ይነካካል፣ ይዳስሳል፣ ያስተውላል፡፡ የሕፃኑ ሙከራና በሂደት የመማሩ እውነታ ይሄው ነው፡፡ ሙከራውና ልምምዱ በሕፃኑ ዕድሜ፣ የዕድገት ደረጃ፣ ጤና፣ ባህልና ሰብዕና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች ይህን የሕፃኑን አዳዲስ ነገሮችን የመሞከርና የመለማመድ ውስጣዊ ፍላጎት፣ ጥረትና ባህርይ በጥንቃቄ ተከታትለን ማገዝ ይጠበቅብናል፡፡

     በተወሰነ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ለምሳሌ የ2 ዓመት ሕፃን ማሳየት የሚኖርበት የተወሰነ ባሕርይ ያለውና በሦስተኛ ዓመት የልደት ቀኑ ደግሞ ተምራዊ በሆነ ለውጥ ወደ ብስለት ይሸጋገራል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው፡፡ እያንዳንዱ ሕፃን ልዩ በመሆኑ መወዳደር ካለበት መወዳደር ያለበት ከራሱ ጋር ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ አፈራረጅ እያንዳንዱን የዕድሜ ክልል የሚወክሉ መሠረታዊ መመሳሰያ ባሕርያት አሉ፡፡ የታዳጊ ሕፃናትን ባሕርያት፣ ፍላጐትና የዕድገት ሂደት ስርዓት መረዳት ለእያንዳንዱ ክፍልና ለእያንዳንዱ ሕፃን ተዛማጅ የሆኑ ዓላማዎችን በቅደም ተከተል ነድፈን የምንተገብረው መርሃ-ግብር እንድናዘጋጅ ይረዳናል፡፡ ሕፃናት ወደ አፀደ-ሕፃናት የሚሄዱበት የዕድሜ ክልል እንደሚኖሩበት አካባቢ ይለያያል፡፡ በአንዳንድ አገሮች በሦስት፤ በአራት፤ በአምስትና በስድስት ዓመታቸው የሚጀምሩ ሲሆን በሌሎች አገሮች ደግሞ ሁለት ወይም በሦስት ዓመታቸው ይጀምራሉ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ አገላለፅ ሕፃናት በሁለት ዓመታቸው አዳዲስ ነገሮችን መማር ይችላሉ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኙ ነገሮችን ያስተውላሉ፡፡ ለአካላዊ እንቅስቃሴያቸው የሚረዷቸውን መራመድንና መሮጥን ይለማመዳሉ፡፡ ከፍ ያሉ ነገሮችን በመያዝ መንጠላጠል ይጀምራሉ፡፡ እንዲህ፣ እንዲህ እያሉም ወደ ሦሰተኛ ዓመታቸው ይሸጋገራሉ፡፡

   በሦስት ዓመታቸው አብዛኞቹ ሕፃናት ቢያንስ መሠረታዊ የመናገር ክሂሎት ስለሚኖራቸው የቃላት ክምችታቸው በየዕለቱ ይጨምራል፡፡ በዙሪያቸው ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ቀስ በቀስ እየተግባቡ መስማማትን መፍጠር ይጀምራሉ፡፡ ማንኛውንም ነገር መመርመር፣ መፈተሸ መሞከር መጠንቆል መቅመስ…ወ.ዘ.ተ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሕፃኑን የማያቋርጥ ቀጣይ እንቅስቃሴ በመገንዘብ ይህን ዕድሜ “የመገስገስ” ዕድሜ ይሉታል፡፡ በእርግጥ ይህ ዕድሜ ሕፃናት የመስማት፣ የመናገር፤ የማስተዋል፣ የመተባበር፣ የመረዳዳት ችሎታዎችንና የእኔነት ስሜቶችን ማዳበር የሚጀምሩበት እድሜ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ሕፃናት የራስ ወዳድነት ባሕርይ ስለሚያጠቃቸው ከሌሎች ሕፃናት ጋር ለመጫወት ያላቸውን ዝግጁነት እምብዛም አያሳዩም፡፡ በዚህም ምክንያት ለብቻቸው የጎንዮሽ ጨዋታ መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ በነፃነት መንቀሳቀስ ስለሚፈልጉ አንዳንዴ የዓዋቂዎችን እርዳታ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ይቃወማሉ፡፡ ወደ አራተኛ ዓመታቸው መሸጋገሪያ ላይ እንደ ግል ባሕሪያቸው ከገደባቸው የመውጣት አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ በመቀጠል ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሕፃናት ተለዋዋጭ ለሆኑት የዕድገት ሂደቶች ተገዢ በመሆን እርስዎን ለማስደሰት የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ይሞክራሉ ፡፡ “አይሆንም/አይደለም” የሚባሉ የእምቢተኝነት ቃላት አሁን “አዎ/አቤት/እሺ” ወደሚሉ ጠቃሚ ቃላት የሚለወጡበት አራተኛ ዓመት የዕድሜ ክልል ተሸጋግረዋል፡፡

     ሕፃናት አራተኛ ዓመታቸው ላይ ሲደርሱ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ እራሳቸውን የመቆጣጠር፣ የመስጠትና የመቀበል ብቃት ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ ድርሻ የመውሰድ፣ የመጋራት ወይም የሌላውን ስሜት የመካፈል ጠባያትን መማር የሚያዳብሩበት እድሜ ነው፡፡ አሁን ከሌሎች ሕፃናት ጋር የመጫወት ፍላጐታቸውና ችሎታቸው እያደገና እየጨመረ መጥቷል፡፡ ስለሆነም የሕፃናት ስብዕና እንዲያብብና ፈክቶ ፍሬ እንዲያፈራ ለሚሞክሯቸው ሙከራዎች ልናመሰግናቸው፣ ልናደንቃቸውና ልናበረታታቸው ይገባል፡፡  ይሁን እንጅ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ግልፅ የሆነ የማሰብ ችሎታቸውን ተጠቅመው ከገደብ የመውጣት አዝማሚያቸውንም በቃላትና በተግባር ይገልፁታል፡፡ እነዚህ ሕፃናት የመማር ወሰኖች ወይም ድንበሮች አሏቸው፡፡ ይህ የዕድሜ ክልል ታላላቅ መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚፈልቁበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ “እንዴት?” እ“ለምን?” የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡበት፣ ለነገሮች መግለጫ፣ ማብራሪያ ወይም መረጃ የሚጠይበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ የአራት ዓመት ሕፃናት በርካታ ተግባራትን ማከናወን ይማራሉ ወይም ለማከናወን ይጥራሉ፡፡ አንዳንዴ ሕፃናት በሥራ ስለሚደክሙ ውጤታቸውንና ደስታ ፈጣሪ ዜናዎቻቸውን ለሚያዳምጣቸው ሰው ሁሉ ማካፈል ይፈልጋሉ፡፡ ከአንደበታቸው የሚወጡ ቃላት “ጉራ በኪሴ” ዓይነት ሰዎች ያስመስሏቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕፃን ስለ ሁኔታው እንዲህ በማለት ለአድማጩ ይገልፃል፡፡ “ተመልከቱኝ! ከዚህ ቅርንጫፍ ላይ መወዛወዝ እችላለሁ!”፣ “ማፏጨት እችላለሁ!”፣ “መስማት ትፈልጋላችሁ? ዛሬ ልብሴን የለበስኩት እኔ እራሴ ነኝ! ማንም የረዳኝ የለም!”  በማለት የአድማጩን ትኩረት ለመሳብ ይጥራል፡፡ ሆኖም ሕፃኑ በሀቅ እየፎከረ አይደለም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ተግባራት ማከናወኑን ወይም ለማከናወን መብቃቱን በእጅጉ ማመን ስላቃተው ነው፡፡ ለሕፃናት “ትልቅ” የመሆን ስሜት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ በዙሪያቸው የተዘጋጁት ነገሮች ሁሉ ለትላልቅ ወይም ለዓዋቂ ሰዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የበርና የመዝጊያ እጀታዎችን፣ ጠረጴዛዎችን ወይም ወንበሮችን ያጤኗል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በመስኮት ወደ ውጪ ለመመልከት ሲፈልጉ ወንበር ላይ ለመንጠላጠል ይገደዳሉ፡፡ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ የማድረጉ ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕፃኑ ሙከራና ጥረት ይበረታታለት፡፡ ይሁን እንጂ የምናደርገው ማበረታቻ ለሁሉም ሙከራዎች አንዴ ብቻ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚደረገው ማበረታቻ እያንዳንዱ አዲስ የተናጠል ጥረት ወይም ሙከራ ከሚያስከትለው ደስታና ከሚደረገው ጥንቃቄ ጋር የተዛምደ መሆን ይኖርበታል፡፡

     ዓመታት እየተቆጠሩና የሕፃናት ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ፍላጎታቸው በሚገርም ሁኔታና እየጨመረና እየሰፉ ይመጣል፡፡ የማሰብ ችሎታቸው ከወትሮው በተለየ መልኩ ይበልጥ በተጨባጭ ወይም በምክንያታዊ ጥያቄዎች የተሞላ ይሆናል፡፡ አሁን ሕፃናት እራሳቸውን ለመቆጣጠር ዝግጁ ስለሆኑ ከዚህ በኋላ ገደባቸውን አይዘሉም፡፡ አሁን የሕፃናት አካላዊ እንቅስቃሴ በሂደት እየተቀናጀ መጥቷል፡፡ በማኅበራዊ ባህርያቸው ተግባራዊ ዕቅዶችን አብረዋቸው በማውጣት የሚተገብሩ የቡድን አባላት አሏቸው፡፡ ሕፃናት ከለፈው ጊዜ በተሻለ ከሁኔታዎች ጋር እራሳቸውን የመለዋወጥና የማጣጣም ባህርይ አላቸው፡፡ እንዲህም እያለ የሕፃናት ዕድገት ይቀጥላል፡፡ በሰባት ዓመታቸው አካባቢ ወደ መደበኛ ትምህርት ይሸጋገራሉ፡፡

2 የሕፃናት ዕድገት መሰላልን መገንዘብ፡-

     ስለ ሕፃናት ዕድገት ሂደት ግንዛቤ ሲኖረን በሥርዓተ-ትምህርቱ ውስጥ የሕፃናት ተሳትፎ ምን መሆን እንዳለበት ፍንትው ብሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሕፃኑ ለጨዋታ የሚጠቀምበትን የሸክላ አፈር ወይም ጭቃ በምሳሌነት እንውሰድ፡፡ ቀደም ሲል በሸክላ አፈር ወይም በጭቃ የመጫወት እድል አግኝቶ የማያውቅ ሕፃን ከጭቃው ወይም ከሸክላው አፈር ጋር የሚገናኝበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ የሸክላ አፈሩን ወይም ጭቃውን ይነካል፣ ይወቅጣል፣ ይወጋል፣ ይበሳል፣ ይደነቁላል፣ ያሸታል…ወ.ዘ.ተ፡፡ ጭቃው ምን እንደሆነና አገልግሎቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ይፈትጋል፣ ይፈቀፍቃል፣ ይጨብጣል ወይም ይጠፈጥፋል፡፡ ቀጥሎም ጭቃ ጠቅልሎ በመቆራረጥ፣ ወይም በማድቦልቦል ወይም በመጠፍጠፍ ኳስ ወይም እባብ መሳይ ቅርፆች መስራት ይጀምራል፡፡ እያንዳንዱን ቁስ አካል ባወቀና በተረዳ መጠን ከልምድ ያገኛቸውን ዘዴዎች በማቀናጀት ተጨማሪ ቅርፆች ይፈጥራል፡፡ የፈጠራውን ሥራ እንዳጠናቀቀ ውጤቱን ያስተውላል፡፡ ውጤቱ ሌላ ነገር የሚያስታውሰው ከሆነ ወዲያውኑ ለውጤቱ ስም ያወጣለታል፡፡ “ተመልከት! ኳስ ሠራሁ” በማለት ውጤቱን ያበስራል፡፡

     በፈጠራው ሂደት ወቅት የሚያገኘው ውጤት ሌላ ነገር ባስታወሰው ቁጥር ስያሜውን ለበርካታ ጊዜ ሊለዋውጠው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሕፃኑ ከፍ እያለና ትንሽ እየበሰለ ሲመጣ ሊሠራ ያሰበውን በቅድሚያ ይወስናል፡፡ ማኅበራዊ ዕድገቱ ይበልጥ እየዳበረ ሲመጣ በቡድን ተደራጅቶ የተለያዩ የስራ እቅዶችን ይወጥናል፡፡ ሕፃኑና ጓደኞቹ ዕቅድን በቡድን በመተግበር ውጤት ለማምጣት ይጥራሉ፡፡ ለምሣሌ በጣም ትንሽ የእርሻ ቦታን በመፍጠር ከሸክላ አፈርና ከጭቃ የተለያዩ የእንስሳት ቅርፆችን ይሰራሉ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ ሕፃን ላልተለመደ ወይም እንግዳ ነገር ያለውን አስተያየት ወይም ምላሽ በማስተዋል ስለ ዕድገቱ ሁኔታ ልንረዳ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕፃን መጀመሪያ አንድን ቁስ በመፈተሽ ምንነቱን ለማጥናት ወይም ለምን እንደሚጠቅም ለማወቅ ይፈልግ ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ሕፃኑ ቁሱን ወደ አፉ ይወስዳል፡፡ በዕድሜ ትንሽ ከፍ ያለው ሕፃን ደግሞ በዕቃው ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ በተለየ ሁኔታ ያወዘውዛል፣ ያንከባልላል፣ ይገፋል፣ ከፍ ዝቅ ያደርጋል ወይም ያንቀሳቅሳል፡፡ የአምስትና የስድስት ዓመት ሕፃን ይህን ቁስ አካል ለይቶ ለመመደብ የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኝ ሕፃን በስሜት ህዋሳቱ አማካኝነት ነገሩ የት እንደሚመደብና ለምን ዓላማ እንደታቀደ ይረዳል ወይም ይገነዘባል፡፡ ቁስ አካሉ አደገኛና ችግር ፈጣሪ ከሆነም፣ ይህንን የማወቅ ችሎታ ስላለው ለመምህሩ ወይም በዙሪያው ላለ ዓዋቂ ሰው ያስረክባል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን አጠቃላዩ የሕፃናት የዕድገት ሂደት መሰረታዊ ተመሳሳይነት ቢታይበትም እያንዳንዱ ሕፃን ከሌላው የተለዬ ስብዕና ያለው መሆኑን እንርሳ፡፡

     እያንዳንዱ ሕፃን ከሌላው የሚለይበት ልዩ ሰብዕና ያለው በመሆኑ ባህርይውን የሚያንፀባርቅበት የራሱ የሆነ መንገድ አለው፡፡ ለምሣሌ ከሌሎች ሕፃናት ጓደኞቹ ጋር እንዴት እንደሚቀላቀልና ትብብር እንደሚፈጥር ልብ ይበሉ፡፡ በአቋሙ የሚፀና ጥብቅ ወይም ግትር ነው? ወይስ ይደራደራል? ስምምነት ላይ ለመድረስ ይጥራል? የሌሎችን አስተያየት ይቀበላል? ያከብራል? ይስማማል? ወይስ የራሱን ሐሳብ ብቻ በሌሎች ላይ ለመጫን ሁልጊዜ ይወተውታል? ወይስ በራሱ መንገድ ብቻ መሄድን ይመርጣል? ወይስ ለሌላ ሀሳብ በቀላሉ እጁን በመስጠት ለመብቱ አይቆምም? እኛ መምህራን ሕፃናትን ይበልጥ ባወቅናቸው መጠን ስለ ሁኔታቸው የመረዳት ዕድል ስለምናገኝ እያንዳንዱ ሕፃን በየትኛው የዕድገት እርከን ላይ እንደሚገኝ ለመገንዘብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርናል፡፡ ለወላጆችም እንደዚሁ፡፡

     ሕፃናት ለወላጆቻቸው የደስታ፣ ፍስሃና ስኬት ምንጭ ሲሆኑ ለሃገራቸው ደግሞ ተስፋና ቃል-ኪዳን ናቸው፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም ምኞትና ተስፋ የሰነቁ በመሆናቸው በአፀደ-ሕፃናት ቆይታቸው ወቅት የመምህራንን ጥበቃና ክብካቤ እያገኙ እንዲማሩላቸው በመፈለግ የሚሳሱላቸውን ልጆች በአደራ መንፈስ ለእኛ ያስረክባሉ፡፡ እምነትም ይጥሉብናል፡፡ እንደ ወላጆቻቸው ሁሉ ሕፃናትም የራሳቸውን ተስፋና ምኞት የሰነቁ ስለሆነ ካልተገደቡ በቀር መማር፣ ማወቅና ውጤታማ መሆን ይሻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሕፃናት ወደፊት ስለሚሆኑት ጉዳይ ማንኛውም ሰው በእርግጠኝነት ሊናገር ወይም ዋስትና ሊሰጥ ወይም ቃል ሊገባ አይችልም፡፡ ሆኖም ለጊዜውም ቢሆን እነኝህ ሕፃናት በእኛ ቁጥጥርና ክብካቤ ሥር ስለሆኑ በምቹ ሁኔታ ላይ በተገነባ የሞቀ ወዳጃዊ ስሜት አስፈላጊውን ዕውቀት ሰጥተንና ኮትኩተን ማሳደግ የእኛ የመምህራን የሥራ ድርሻ ስለሆነ አንዳንዴ የቡድን አስተምህሮት ዘዴን፤ አንዳንዴ ደግሞ የአንድ ለአንድ ያስተምህሮት ዘዴን እንጠቀም፡፡ ይህን ከመተግበራችን በፊት ግን ከምንም በላይ ስለ ሕፃናት ጠንቅቀን ማወቅ የሚገቡንን እውነታዎች መረዳት ወይም ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ መሰረታዊ ሀሳብ ድጋፍ የሚሆኑን ትምህርታዊ ዕወነታዎች ታዋቂዋ የቶለራንስ ካሊፎርኒያ ሄራልድ ጋዜጣ አምደኛ ዶርቲ ሎውናታል እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም “Creative Family Living” በሚል ርዕስ ስር ያሰፈረቻቸውን ምክሮች ማጤኑ በጣም ጠቃሚ ነው እላለሁ፡፡    

 • አንድ ሕፃን ከወቀሳና ትችት ጋር ካደገ፣ ማውገዝንና መንቀፍን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን በፍርሃትና ስጋት ውስጥ ካደገ፤ ጭንቀትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከጥላቻ ጋር ካደገ፣ ጠብን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከሐዘንና ፀፀት ጋር ካደገ፣ በራሱ ላይ እያዘነ መኖርን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን እየተፌዘበት ካደገ፤ ዓይን አፋርነትን፣ ድንጉጥነትንና ደንጋራነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከቅናት ጋር ካደገ፤ ምቀኝነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከሀፍረትና ውርደት ጋር ካደገ፤ ጥፋተኛነትንና ሃጢያተኛነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን እየተበረታታ፣ እየተደፋፈረና እየተነቃቃ ካደገ፤ በራስ መተማመንን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከትዕግስትና መቻቻል ጋር ካደገ፤ ቻይነትንና ጥንቁቅነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከምስጋና ጋር ካደገ፣ ማድነቅን  ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከተደማጭነት ጋር ካደገ፣ አፍቃሪነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከመፍቀድና ማፅደቅ ጋር ካደገ፣  እራስን መውደድና መቀበልን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ዕውቅና ከማግኘት ጋር ካደገ፣ የዓላማ ጠቃሚነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ያለውን ከማካፈልና ከመረዳዳት ጋር ካደገ፣ ደግነትን፣ ቸርነትን ወይም ለጋስነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከቅንነት፣ ታማኝነትና ሚዛናዊነት ጋር ካደገ፣ እውነተኛነትና ፍትሃዊነትን ይማራል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከመልካም አያያዝና ደኅንነት ጋር  ካደገ፣ በራሱና እርሱን በተመለከቱ ጉዳዮች እምነት ይኖረዋል፡፡
 • አንድ ሕፃን ከወዳጃዊ አቀራረብና ጨዋታ ጋር ካደገ፣ ዓለም ምቹ የመኖሪያ ስፍራ መሆኗን ይማራል፡፡
 • እርስዎ ከመንፈስ እርካታ ጋር የሚኖሩ ከሆነ፣ ልጅዎ በሰላማዊ አእምሮ ውስጥ ይኖራል፡፡

     ለመሆኑ የልጆቻችን ህይወት በየትኛው ሁኔታ ወይም ዕውነታ ውስጥ ይገኛል? ሕፃናት የሚያንፀባርቋቸው ባሕርያት በአብዛኛው በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ባለው ሕይወት ተፅዕኖ ሥር የወደቁ ናቸው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ፣ ልብስ፣ ጥበቃና እንክብካቤ ያገኛሉ? በቂ እንቅልፍስ ይተኛሉ? እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ አካባቢያዊ ሁኔታዎች በሕፃናት ባሕርያት ይንፀባረቃሉ፡፡ የማንኛውም ሕፃን ባሕርይ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተገናኘና የተዛመደ ነው፡፡ ይህም ማለት ሕፃኑ የዕድሜውን ይተውናል፣ ያከናውናል ወይም ይተገብራል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለሕፃናት ርኅሩኅ፤ ደግና ቸር እንሁንላቸው፡፡ በአክብሮትና ጨዋነት እንከባከባቸው፡፡ እያንዳንዱ ሕፃን የመከበርና የተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ለጤናማ እድገቱ በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በምንም ምክንያት በየአጋጣሚው ሁሉ ማፌዝ፣ ማላገጥ ወይም ሕፃኑን ማሳነስ፣ ማንኳሰስና በሕፃኑ ላይ አላስፈላጊ ድርጊቶችን መፈፀም እኩይና ክፋት የተሞላበት ተግባር ነው፡፡ በሕፃናት መካከል አድሏዊ ከመሆን እንቆጠብ፡፡ ሁልጊዜም ግልፅና ሚዛናዊ መሆናችንን እናሳያቸው፡፡ ሕፃናት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ሁሉ ግልፅ፤ ቅን፣ ታማኝ፣ ለዕድሜያቸውና ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ ተስማሚ የሆኑ መልሶች መመለስ ከእኛ ከመምህራንና ወላጆች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የገባንላቸውን ቃል ማክበር ወይም በወቅቱ መፈፀም የማንችል ከሆነ ከመጀመሪያውኑ ባንሞክረው ይመረጣል፡፡ ሕፃናት በቀላሉ የሚያምኑና የሚታለሉ ናቸው፡፡ ሕፃናት በስርዓት ሲያዙ፣ ሞቅ ያለ አቀባበልና እንክብካቤ ሲደረግላቸው መልካም ባሕሪያትን በመማር ተመሳሳይ ጠባያትን ያንፀባርቃሉ፡፡ ለሕፃናት እንክብካቤና ድጋፍ የምናደርግ ሰዎች ሁሉ በሕፃናት ሰብዕና ላይ የበኩላችንን ሚና የምንጫወት ሰዎች ስለሆን የሕፃናትን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረፅ ረገድ ጉልህ ተፅዕኖ የምናሳድር መሆናችን መረዳት ይኖርብናል፡፡ መምህራን በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ ስንሰራ ከፍተኛ የሙያና የሞራል ኃላፊነት የተሸከምን ስለመሆናችን ለአፍታም አንዘንጋ፡፡

     የአፀደ-ሕፃናት መምህራንና የሕፃናት ተንከባካቢዎች መሆናችን ወይም ለመሆን ማሰባችንና ሕፃናትን መውደዳችን ሕፃናት ከእኛ ጋር በሚሆኑ ወቅት ተደስተውና አእምሮአዊ መነቃቃት አግኝተው በግቢያችን ውስጥ እንዲቆዩ ይረዳቸዋል፡፡ የሕፃናትን ባሕርያት ይበልጥ እየተረዳን በሄድን ቁጥር እነርሱን ለመምራት ወይም አቅጣጫ ለማስያዝ ብቁ እንሆናለን፡፡ ስለ እያንዳንዱ ሕፃን ቤተሰባዊ መሠረት፣ ያለፈ ታሪክና ልምድ የምንችለውን ያህል ለማወቅ ጥረት በማድረግ የሕፃኑን ሁኔታ ይበልጥ ለመረዳት እንጣር፡፡ ከሁሉም በላይ ጠቃሚው ነገር በእኛ ክብካቤ ሥር የሚገኙ ሕፃናት ከእኛ ጋር በሚሆኑበት ወቅት የደህንነትና ምቾት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከአሳዳጊዎቻቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው ሲነጠሉ ለአብዛኞቹ ሕፃናት የመጀመሪያ ተሞክሯቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሕፃናት በአዲሱ ሁኔታና አካባቢ እርግጠኛ ስለማይሆኑ ይፈራሉ፡፡ በአፀደ ሕፃናት ቆይታቸው ከሚያገኟቸውና ከሚነካኳቸው ነገሮች ይልቅ በቅድሚያ ከለላና እንክብካቤ ይፈልጋሉ፡፡

     ሕፃናት የመጡበት ቤተሰብ የቅርብ ግንኙነት የተጠናከረበትና ፍቅር የሰፈነበት ከሆነ አዲሱን አካባቢ ተቀብሎ ከሌሎች ለመቀላቀልና ለመዋሐድ የተሻለ ዝግጁነት ሊኖራቸውና ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ በቤታቸው ውስጥ ያሳለፉት ምቹ የሕይወት ቆይታና ያገኙት ልምድ ዓለም አመቺ የመኖሪያ ቦታ መሆኗን፤ ሌሎችንም ማመን የማይጎዳና ጠቃሚ ጉዳይ መሆኑን እንዲያምኑ ይረዳቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ዘወትር ገደብየለሽ ቅጣትን፣ መከፋትንና ቅሬታን ማስተናገድ ባህሉ ከሆነ ቤተሰብ ውሰጥ የመጡ ሕፃናት መጀመሪያ እርስዎንና አዲሱን አካባቢ ሊጠራጠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ወቅት ለእነዚህ አይነት ሕፃናት ከፍተኛ ትዕግስት ሊኖረንና የምንችለውን ያህል የጋለ ፍቅርና መረጋጋት ልንለግሳቸው ይገባል፡፡ ሦስት እጅ የሆነውን የሕፃናት ደህንነትና ክብካቤ ተግባራችንን በአፀደ ሕፃናታችን ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናት በበርካታ መንገዶች ማስፈን ይቻላል፡፡ እነዚህንና መስል ጉዳዮችን ይዤ በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ አዲሱ ዓመት መልካም መምህራንና መልካም ወላጆች በመሆን የልጆቻችንን ጤናማ ሰብዕና የምንቀርፅበት፣ የሞራል ብቃታችንን የምናድስበትና የምንደሰትበት ዓመት ይሁንልን እያልኩ እሰናበታለሁ፡፡

መልካም መልካሙን ለሕፃናት!!!

መምህር ሣህሉ ባዬ

 (MA in Chid Development, BA in Pshychology,

MBA & IDPM in Project Management)

Email: sahilubaye@gmail.com and/or ecd@ethionet.et   

      www.enrichmentcenters.org


 • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”