call us now

251 1 911 23 08 57 / 60 76 06

Learning is power Part Three

የነገውን ሰው ማነጽ - ይድረስ ለወላጆችና መምህራን

(ክፍል 3)

ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ በሕፃናት አስተዳደግ ላይ የመምህራንን ሚና አስመልክቼ አንድ፤ ሁለት……ነጥቦች በማንሳት ሙያዊ ምልከታየን ለአንባብያን ማድረሴ ይታወሳል፡፡ በዛሬዋ መልዕክቴ ደግሞ የወላጆችና የመምህራን ሦስት እጅ የዕለት-ተዕለት ተግባር በሆነው የሕፃናት ደህንነትና እንክብካቤ ላይ አተኩራለሁ፡፡ በያላችሁበት ደህንነታችሁ የተጠበቀ እንዲሆንላችሁ እየተመኜሁና ዕለታዊ ሰላምታዬን እያቀረብኩ ከዘርፉ ባሙያዎች የተገኙ ስነልቦናዊና ፔዳጎጅካዊ ምክሮችን እንደሚከለተው አቀርባለሁ፡፡

ሕፃናት ጥበቃና ደህንነት ይፈልጋሉ !!    

የደህንነት ስሜትና ጥበቃ ለሕፃናት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሕፃናት በት/ቤት ውስጥ ከሚያገኟቸው የመጫወቻ ዕቃዎች ይበልጥ ከለላና እንክብካቤ ይሻሉ፡፡ ይህን መሠረታዊ የሕፃናት ፍላጎት ለማሟላት የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን ጠቃሚ ነው፡፡

ግልፅ ሆኖ የተዋቀረ ቁስ አካላዊ አካባቢ፡- አንድ አፀደ-ሕፃናት ግልፅ ሆነው በተዘጋጁ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች መደራጀት ይኖርበታል፡፡ በክፍል ውስጥ የሚገኙ ዕቃዎች ቦታቸውን በአግባቡ ካገኙ ክፍሉ ምንጊዜም ለሕፃናት መልክና ሥርዓት ያለው ሆኖ ይታያቸዋል፡፡

መለየት፣ ማገናኘት ወይም ማዛመድ ይችሉ ዘንድ የተለያዩ ቁሶችን መስጠት፡- ሕፃናት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ ሲውሉ የሚያገኟቸው ነገሮች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከሚገኙ ነገሮች ጋር የሚመሳሰሉ ከሆነ ይበልጥ ምቾት ይሰማቸዋል፡፡ ለምሣሌ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ማሰሮ፣ ወንፊት፣ ትራስ፣ ከሳር ወይም ሰንበሌጥ የተሠራ ሰሌን (የወለል ምንጣፍ)፣ ሳጥን፣ በርጩማ፣ ሙዳይ…..ወዘተ ከሚጠቀሱት ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በገጠር ለሚገኙ ሕፃናት የእርሻ እንስሳትን አስመስሎ ከቆሮቆንዳ፣ ከሳርና ከሰንበሌጥ በመሥራት ሕፃናት በጨዋታ ጊዜያቸው እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ ለጨዋታና ማስተማሪያነት የምንመርጣቸው ነገሮች አፀደ-ሕፃናቱ እንደሚገኝበት አካባቢ የሚወሰን ይሆናል፡፡

በቅደም-ተከተል የተቀረፀ የተግባር መርሃ-ግብር፡- ሕፃናት በቅደም-ተከተል ተዘጋጅተው በት/ቤት ውስጥ ከሚያከናውኗቸው ድርጊቶች ጋር ሲላመዱ ተረጋግተው በቀጣይ ምን ማከናወን እንደሚችሉ የማወቅ ስሜት ያዳብራሉ፡፡ የመድረሻ፣ የመሰብሰቢያ፣ የመማሪያ፣ የመፀዳጃ፣ የመመገቢያ፣ ወደ መኖሪያ ቤት የመመለሻ ውሱን ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ ጐልቶ የሚታይ የዕለታዊ እንቅስቃሴ ድግግሞሽ ለሕፃናቱ የደህንነትና የቀጣይነት ስሜት ይፈጥርላቸዋል፡፡ ሕፃናት በቀጣይ ምን እንደሚከሰት በቅድሚያ ማወቃቸው የደህንነትና ምቾት ስሜት እንዲሰማቸው የሚረዳቸው ቢሆንም ለሕፃናት አእምሯዊና አካላዊ እድገት ተመጣጣኝ ያልሆኑ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ማስገደድ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ መምህራንና ወላጆች ለሕፃናት የምናስተላልፈው ትምህርትና መመሪያ ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሣሌ “ጧት ጧት ወደ ት/ቤት ስትመጡ እባካችሁ ልብሳችሁን ለእያንዳንዳችሁ በተመደው ቦታ ላይ አስቀምጡ፡፡ ይህን ካደረጋችሁ በሁዋላ ጓደኞቻችሁ ጋር መቀላቀል ትችላላችሁ፡፡ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ የፅዳት ክፍለ ጊዜ ይሆናል፡፡ አካባቢያችሁን ካፀዳችሁ በሁዋላ ደግሞ መጽሐፍ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡” በማለት ማቅረብ ይቻላል፡፡ በዚህ ቅደም-ተከተል መሠረት የተዋቀሩ ተግባራትን ሕፃናት በቅድሚያ ከተገነዘቡ ዕለቱ የተረጋጋና አስደሳች ይሆንላቸዋል፡፡

ሥነ-ሥርዓት፡- የሕፃናት ጠባይ ትክክለኛ መስመር እንዲይዝ የመምራትና አቅጣጫ የማሳየት ጉዳይ ነው፡፡ የሥነ-ሥርዓት ደንቦችን ከቀረፅን በሁዋላ ለተግባራዊነታቸው በአቋማችን መፅናት ይጠበቅብናል፡፡ እንደሚከተለው የሰፈሩት ነጥቦች በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ ሕፃናት ደንቦች ስለሚያስፈልጋቸው ለማኅበረሰብ የደህንነት ከለላ ለመስጠት ሲባል ሕግጋትና ደንቦች እንደሚቀረፁ ሁሉ የአፀደ-ሕፃናት መማሪያ ክፍልም ልክ እንደ አንድ ትንሽ የኅብረተሰብ አካል በመሆኑ መምህራን በእንክብካቢያችን ሥር ለሚገኙ ሕፃናት የሚያገለግሉ የሥነ-ሥርዓት ደንቦች ቀርፀን መተግበር ይኖርብናል፡፡ ሆኖም ቀርፀን የምንተገብራቸው ደንቦች ምክንያታዊና ውጤታማ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ለምሣሌ -

ደንብ - “ለማዳና አጫዋች እንስሳትን ስትይዝ በእርጋታ ያዛቸው፡፡”

ምክንያት- “ከጨመደድካቸው ወይም ከተጫንካቸው…..”

ውጤት -“ይጎዳሉ፡፡”

ሕፃናት ከደንቦች ጀርባ የሚገኙ ምክንያቶችን ከተረዱ ለመቀበልና ለመታዘዝ ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ አመላካች ጥያቄዎችን በመጠቀም የደንቦችን አስፈላጊነት እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ “ለማዳና አጫዋቹን እንስሳ ጨምድደን ብንይዘው ምን ይሆናል?” በማለት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ እንስሳን ጨምድዶ መያዝ ሊጎዳው እንደሚችል ሕፃናት ስለሚረዱ ለጥያቄው በቀላሉ መልስ መስጠት ይችላሉ፡፡

ሕፃናት ወደትክክለኛው ባሕርይ እንዲመጡ፡- በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ አንዳንድ ሕፃናት ቁጥጥርና ገደብ መኖሩን ቢረዱም አንዳንዴ ወደማይፈለግ ጠባይ ሊሻገሩ ይችላሉ፡፡ በሚፈጠርባቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳቢያ ባልተለመደ ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው አመል ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ይህን የማይፈለግ ጠባይ እንዲያንፀባርቁ ከሚያስገድዷቸው ሁኔታዎች መካከል አንደኛው ከበርካታ ልጆች ጋር ሲውሉ የመጀመሪያቸው መሆኑና ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ሲል ከሌሎች ሕፃናት ጋር ተቀላቅለው የመዋል ልምድ ስላልነበራቸው ነው፡፡ ሕፃናት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተለመዱ እንደ መነጫነጭ፣ መቅበጥበጥና የመሳሰሉ አመሎችን በማንፀባረቅ ወደማይፈለጉ ባህርያት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ አንድ ሕፃን የማይፈለግ አመል ሲያሳይ ጠቃሚውና ተገቢው መንገድ ሕፃኑን ሳይሆን አላስፈላጊውን አመል መንቀፍ ወይም ማውገዝ ነው፡፡ ከስህተቱ እንዲማር መሞከር ተገቢ ነው፡፡ ለምሣሌ ዘነበች በቁርጥራጭ ድንጋዮች ሕንፃ እየገነባች ነበር እንበል፡፡ አበበች ደግሞ ድንጋይ በመያዝ ዘነበች ወደምትሰራው ሕንፃ በመጠጋት ድንጋይ በመወርወር ዘነበች የሰራችውን የሕንፃ መዋቅር በታተነችው እንበል፡፡ በዚህ ጊዜ ለአበበች እንዲህ በማለት ሁኔታዎችን ማስተካከል ይችላል፡፡ “አበበች ድንጋዮች ሕንፃ ለመሥራት እንጂ ለውርወራ አያገለግሉም፡፡ እባክሽ! ዘነበችን ይቅርታ ጠይቂያትና ሕንፃውን መልሶ ለመገንባት እርጃት››፡፡ ይህ አቀራረብ “አንቺ መጥፎ ልጅ!” ከሚለው አቀራረብ በእጅጉ ተመራጭ ነው፡፡ አንዳንዴ አንድን ግንባታ ማፍረስ ወይም መረበሽ ሕፃናት አስበውበት የሚያከናውኑት ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አልማዝ በመማሪያ ክፍሏ በአሻንጉሊቶች ማዕዘን አካባቢ የአሻንጉሊቶቿን ልብሶች የምታጥብበት ውሃ በጎድጓዳ ዕቃ ይዛለች እንበል፡፡ ጎድጓዳ ዕቃውን እስከ አፉ ሞልታ በመያዝ የፅዳት ሥራዋን ለመጀመር በጥድፊያ ላይ እያለች ሕፃን አበባ ከቤት በመውጣት ላይ መሆኗን አልማዝ ባለማስተዋሏ በድንገት ተጋጩ እንበል፡፡ እንደተጋጩም አብዛኛው ውሃ በልብሶቻቸውና በወለሉ ላይ ፈሰሰ እንበል፡፡ ይህ ዓይነት አጋጣሚ ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል አልማዝን እንዲህ በማለት መርዳት እንችላለን፡፡ “አልማዝ ጎድጓዳውን ዕቃ ከበቂ በላይ በውሃ ሞልተሽው ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ውሃው እንዳይፈስ ምን ማድረግ አለብሽ?” ብለን በመጠየቅ ችግሩን ማሳየት እንችላለን፡፡ በመቀጠልም “በሚቀጥለው ጊዜ ምን ታደርጊያለሽ…?” የሚል ጥያቄ በማቅረብና ሐሳቧን በመረዳት የአልማዝን የወደፊት የተግባር አቅጣጫ መምራት እንችላለን፡፡ ይህንን ተከትሎ ሁለቱም ልጆች ልብሶቻቸውን እንዲያደርቁና አልማዝም በወለሉ ላይ የፈሰሰውን ውሃ እንድታፀዳ መታዘዝ ይኖርባታል፡፡ እኛ ወላጆችም ሆን መምህራን አልማዝ የተሰጣትን ትዕዛዝ ተቀብላ ለመተግበር የምታሳየውን ፍላጐት የምናደንቅላት መሆናችንን በማበረታቻ ቃላት ልናረጋግጥላት ይገባል፡፡ አልማዝ በቀጣይ ለሥራዋ ትኩረት ሰጥታ በጥንቃቄ ማከናወን እንዳለባት ማስገንዘብም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ሂደት መተላለፍ ያለበት ይበልጥ ትምህርታዊ በሆነ መንገድ እንጂ “አንቺ ቀርፋፋ፣ የማያምርብሽ፣ የማይሆንልሽ! በመንገድሽ ላይ ምን እያየሽ ነው የምትደናበሪው?” የሚሉ ስድቦችና በብስጭት የታጀቡ አላስፈላጊ ንግግሮችን መጠቀም በሕፃናት የሰብዕና እድገት ላይ የሚኖሯቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡

በጓደኞች ፊት የሚሰነዘሩ ቁጣዎችና ግሳፄዎች፡- ምናልባት አንድ ሕፃን የማያስፈልግ ጠባይ የሚያሳይ ከሆነ ከጓደኞቹ ራቅ አድርገን በግል ማነጋገር መልካም አቀራረብ ነው፡፡ አንዳንዴ ምክር ፈላጊውን ሕፃን ራቅ ወዳለ ሥፍራ መውሰድ ወደ እንቅስቃሴው ተመልሶ ሲመጣ ሁኔታውን ተረጋግቶ እንዲከታተል ይረዳዋል፡፡

ጠቃሚ አባባሎችን መጠቀም፡- አንድ ሕፃን ሊሞክረው ወይም ሊሰራው የሚገባውን ተግባር ማመላከት ተመራጭ ነው፡፡

ለምሣሌ፡-

     ሀ. መምራት የሚያስችሉ አገላለፆች፡-

“ከተረቱ በኋላ ምን አይነት ነገር እንደሚከተል ለማወቅ እናዳምጥ፡፡”

“ቁርሳችንን መብላት እንደጨረስን ለጨዋታ ከክፍል ውጪ እንወጣለን፡፡”

“ለእያንዳንዱ የቀለም ዓይነት ራሱን የቻለ ብሩሽ ተጠቀሙ፡፡ ቀለማት ለረዥም ጊዜ ብሩህ ሆነው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡”

     ለ. መምራት የማያስችሉ አገላለፆች ፡-

“ታሪክ እያነበብን ስለሆነ አታውራ፡፡”

“የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ስላልሆነ ወደ ውጪ ወጥታችሁ መጫወት አትችሉም፡፡”

“ቀለማት ያጨቀያሉና ሁሉንም ብሩሾች ቀለም ውስጥ አትንከሯቸው፡፡”

ነፃነትና መብት፡- የሕፃናትን ነፃነት መሠረታዊ መብቶች ማክበር አስፈላጊ ቢሆንም ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ይህም ማለት ለሕፃናት የሚሰጡ መሠረታዊ የነፃነት ሰባዓዊ መብቶች አስፈላጊ መሆን አጠያያቂ ባይሆንም የነፃነት ደረጃ አንፃራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሕፃናት ውሳኔ አሰጣጥን እንዲማሩ ምርጫዎችን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በዚህም መሰረት የእኛ የሥራ ድርሻ የአማራጮቹን መጠን መወሰንና ተቀባይነት ያላቸውን አማራጮች ብቻ ማቅረብ ይሆናል፡፡ በመቀጠል በማዕቀፍ ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንፍቀድላቸው፡፡ ለምሣሌ ሕፃናት ያለ ቤተሰባዊ ቁጥጥር ከቤት ውጭ ሊንቀሳቀሱ አይችሉም፡፡ በክፍልም ውስጥ ሌላውን ሕፃን መጉዳት ወይም የሌላውን ሕፃን እንቅስቃሴ ማወክና ማደናቀፍ መብት የላቸውም፡፡ ስዕሎችን ቀለም መቀባት፣ በቁርጥራጭ እንጨቶች ህንፃ መገንባት፣ ቀለማትን ማዛመድ…..ወዘተ በነፃነት የሚተገበሩ ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት በመማር-ማስተማር ሂደት ውስጥ መልካም አማራጮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የትኞቹንና ምን ያህሎቹን አማራጮች መፍቀዳችን የሚወሰነው በእኛ እንክብካቤ ሥር ባሉ ሕፃናት ብዛት፣ ኃላፊነትን በተሸከሙ ዓዋቂ ሰዎች ቁጥር፣ አመቺና በቂ ቦታ መኖርና ሕፃናትን የመውደድ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡

አንዳንዴ ምርጫዎች የማይገኙባቸው ሁኔታዎች አሉ፡- እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ሕፃናትን ማስጎምዠት አይኖርብንም፡፡ ለምሳሌ ሕፃናት በክፍል ውሰጥ የቀለም ቅብ፣ የማጣበቅና የሌሎች ተጨማሪ ተግባራት ክፍለ ጊዜ በቅርቡ ነበራቸው እንበል፡፡ አሁን ደግሞ የማፅዳትና የተበታተኑ ዕቃዎችን ወደ ቦታቸው መልሶ በስርዓት የማስቀመጥ ጊዜ ነው እንበል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ “አሁን ማፅዳት ትፈልጋላችሁ?” በማለት ብንጠይቃቸውና አብዛኞቹ “አንፈልግም!” የሚል መልስ ቢሰጡን አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ በነገራችን ላይ ጥያቄው “እንፈልጋለን” ወይም “አንፈልግም” ለማለት ግልፅ ምርጫ የሚሰጥ ነው፡፡ ጊዜው የፅዳት ጊዜ በመሆኑ በጥያቄ መልክ ያልቀረበ ቀለል ያለ አነጋገር ቢሆን ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ “አሁን የማፅዳትና የተበታተኑትን ዕቃዎች ሰብስቦ ወደ ቦታቸው በመመለስ በስርዓት የማስቀመጥ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡” በማለት መልዕክቱን ማስተላለፍ ተገቢ አቀራረብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “ሕፃናት አሁን አሸዋ መበተን የለብንም” በማለት ከተናገርን በኋላ “መበተን አለብን እንዴ?” የሚል ጥያቄ ካቀረብን “አዎ መበተን አለብን!” ለሚል ምላሽ ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ስለሆነም በመጀመሪያ ካቀረብነው መልካም አባባል ጋር ጥያቄ በማስከተላችን ችግሩ እንዲከሰት አድርገናል፡፡

ለሕፃናት የሚኖረን አቀራረብ፡- ከሕፃናት ጋር ስንነጋገር ለስላሳ ወይም ረጋ ያለ ድምፅ መጠቀም ጠቃሚ ነው፡፡ ሕፃናት የሚማሩት በምሣሌ ነው፡፡ ወላጆችና መምህራን ለሕፃናት ነገሮችን አዛምደን የምንገልፅበትና ለዛ የተላበሰ አቀራረባችን ሕፃናት በመደበኛ የመማር-ማስተማር ሂደት ውስጥ ከሚያገኙት ዕውቀት ያላነሰ ያስተምራቸዋል፡፡ ታጋሽነታችን፣ ደስተኛነታችንና ሕፃናትን መውደዳችን ከሕፃናት ጋር መግባባትን ይፈጥርልናል፡፡ ሕፃናት ለእኛ በጣም ጠቃሚ መሆናቸውን እናሳያቸው፡፡ እያንዳንዱ ሕፃን መምህሩና ወላጆቹ የእርሱ ተንከባካቢ መሆናቸውን እንዲረዳና በተለየ ሁኔታ ተፈላጊ ሰው መሆኑ እንዲሰማው ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ከሕፃናት ጋር ባለን የዕለት-ተዕለት ግንኙነት እያንዳንዱን ሕፃን በስም ጠርተን የምናነጋግርበት ጊዜ ይኑረን፡፡ አንድ ወይም ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን ለሕፃኑ መወርወር በመካከላችን ሞቅ ያለ ግንኙነት ለመፍጠር በጣም ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ “ናስር እንደምን አደርክ? ትናንትና አጣንህ? አሞህ ነበር?” “ሄርሜላ ምን ዓይነት ውብ ጫማ ነው የተጫማሽው? ይመቻል?” በማለት ለተወሰነ ጊዜ ማነጋገር ጠቃሚ ነው፡፡ ከአካባቢያችን ባህል ጋር የማይጋጭብን ከሆነ ከሕፃናት ጋር ስንወያይ በተቻለ መጠን ወደ ሕፃናቱ ዓይኖች ጐንበስ ወይም በርከክ በማለት ፊት-ለፊት እያየን እናነጋግራቸው፡፡

ሕፃናት ስኬታማ የመሆን ስሜት እንዲሰማቸው የምንፈልግ ከሆነ አቅጣጫ ማስያዝ የወላጆችና የመምህራን ተግባር ነው፡፡ አንዳንድ ሕፃናት የተለዩ ተግባራትን ለማከናወን ድጋፍ ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ድንጉጥና ዓይን አፋር ሕፃን ሊበረታታና ሊደፋፈር ይገባዋል፡፡ ረባሽ፣ ዐመፀኛ ወይም ሥርዓተ-አልበኛ የሆነ ሕፃን መረጋጋትን እንዲማርና እንዲለማመድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሕፃን ደንታ ቢስ፣ ሞገደኛ፣ ጠበኛ ወይም አምባጓሮኛ የመሆን ጠባይ ሲያንፀባርቅ ስብዕናው በስርዓት አለመቀረፁን ያሳያል፡፡ ምንአልባት በክፍል ውስጥ ለሕፃኑ የተሰጠው ተግባር አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበት ወይም ቤተሰባዊ ችግር ኖሮበት ወይም ሌላ ችግር ገጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕፃናት ስኬታቸውን እንዲያውቁ ችሎታቸውንና አቅማቸውን ያገናዘቡ ተግባራት እንስጣቸው፡፡ በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን በትኩረት መከታተላችን ለእያንዳንዳቸው የሚሆን ተስማሚ ተግባር አዘጋጅተን መቅረብ እንድንችል ይረዳናል፡፡ ሕፃናት ሊያከናውኗቸው ወይም ሊማሩባቸው  የሚችሉ ተግባራት ሁሌም ሊኖሩን ይገባል፡፡ ይህንን ካላደረግን ግን ሕፃናት ዕረፍት የለሽ፣ ቁንጥንጥና ስልቹ ይሆኑብናል፡፡ ስለሆነም ዝግጅቱ ቀደም ብሎ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ከሕፃናት ጋር ስንሆን ትኩረታችን በሙሉ በሕፃናቱ ላይ እንጂ ነገሮችን በማስተካከል የተጠመድን መሆን የለብንም፡፡ አስፈላጊ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ከክፍለ ጊዜው ቀደም ብለን ለሥራ ዝግጁ እናድርጋቸው፡፡

የሕፃናት ደህንነት፣ ት/ቤትና መልካም ቤተሰባዊ ግንኙነት፡- አፀደ-ሕፃናትን ለማደራጀት ወይም ለማዋቀር የምንፈልግ ከሆነ ከምናስበው በላይ በርካታ መንገዶች ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ወጥ የሆነ አደረጃጀት የለም፡፡ አብዛኞቹ አፀደ ሕፃናት በአካባቢያቸው ሁኔታ ላይ ተመስርተው የተዋቀሩ ናቸው፡፡ የእርስዎ አፀደ-ሕፃናት የሚገኘው ሰው በበዛበትና በተጨናነቀ የከተማ መኖሪያ ስፍራ ውስጥ ነው? ወይስ ሰፊ ቦታ ባለው የገጠር አካባቢ? ከመደብር የሚገዙ ትምህርታዊ ዕቃዎችና መሳሪያዎችን የማግኘት ዕድል አለዎት? ወይስ ተፈጥሮ የለገሰችዎት እንደ እንጨት፣ ቀርከሃ፣ ድንጋይ፣ ተክሎች የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ሃብቶች? አዲስ አፀደ-ሕፃናት እየመሠረቱ ከሆነ ያልተነካ ወይም ያልተጎዳ ተፈጥሮዊ አካባቢን በተቻለ መጠን ከልሎና ጠብቆ ማቆየት ብልህነት ነው፡፡ በተጨማሪም አፀደ-ሕፃናታችን ከሕፃናት መኖሪያ ሰፈር ብዙ ሳይርቅ በአጭር የጉዞ ርቀት ላይ የተደራጀ ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ ሕፃናት አድካሚ ርቀት የሚጓዙ ከሆነ ወደ አፀደ-ሕፃናታችን ላይመለሱ ይችላሉና የት/ቤቱን አቀማመጥ ማጤን ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ከሌላው ተራርቆ በሚኖሩበት የገጠር ቤተሰብ አሰፋፈር የጉዞ ጊዜን ትኩረት ሰጥቶ ማቀድ አስፈላጊ ነው፡፡ አፀደ-ሕፃናታችን የትም ይሁን የት፣ መጠኑና ስፋቱ ምንም ይሁን ምን በአእምሯችን ተገቢ ስፍራ ማግኘት የሚገባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች በቀጣይ መጣጥፌ እስከምመለስባቸው ድረስ ለዛሬ የሕፃናት የደህንነት ስሜት መሠረት የሚጣለው መጀመሪያ በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ስለሆነ ሕፃናት ወደ ት/ቤት ከመሄዳቸው በፊት ወላጆች ማወቅ የሚገባቸው አንድ፣ ሁለት ነጥቦችን እዚህ ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ውሏቸውን ስለሚያሳልፉባቸው አፀደ-ሕፃናትና በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ ስለሚያበረክቷቸው መልካም ተግባራት ቀድመው እንዲያውቁ ማድረግ የወደፊት ተሳትፏቸው ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ባለፍው መልዕክታችን መጠቆማችን ይታወሳል፡፡ ስለሆነም በተወሰነ ጊዜ ወላጆችን የሚያሳትፉ የውይይት ፕሮግራሞች አቅዶ መተግበር ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በውይይት ሂደት ቀለል ያሉ የኅትመት ውጤቶችን ማሰራጨትና መረጃዎች ለእያንዳንዱ ወላጅ እንዲደርሱ ማድረግ ይቻላል፡፡ የፊልም፣ የስላይዶችና የሚና ጨዋታ ፕሮግራሞችንም ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ በወላጆች መካከል የሚደረግ ውይይት አንዱ ከሌላው የሚማርበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በሁኔታዎች ብቻቸውን አለመሆናቸውን ይገነዘባሉ፡፡ አምቀውና ተጭነው የያዟቸውን ሐሳቦች፣ ስሜቶች፣ ፍላጎቶች፣ ችግሮች…ወ.ዘ.ተ ለሌላ ሰው ስለሚያካፍሉ እኛ ከእነርሱና ስለ እነርሱ የመማር ዕድል ይኖረናል፡፡ ስለ ሕፃናት የሁዋላ ታሪክና ልምድ ቀድመን ግንዛቤ ካገኘን ውጤታማ ስራ መሥራት እንችላለን፡፡

ወላጆችን አጅበን ወደ ውይይቱ መድረክ ስናመጣቸው እግረ መንገዳችንን ስለ አመጋገብ ዘዴ፣ ስለ ሕፃናት አስተዳደግ፣ ስለ ልዩ ፍላጎት፣ ስለ ልዩ ችግሮች (አልጋ ላይ ስለመሽናት፣ ጣት ስለመጥባት፣ ዘግይቶ ስለመተኛት) እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የበኩላችንን ሙያዊ አስተያየት እንስጣቸው፡፡ ምናልባትም አንዳንድ ወላጆች ተመሳሳይ ችግሮቻቸውን በጨዋታ ወይም በቀልድ መልክ ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ማድረግ የሚቻል ከሆነ በቡድን ውይይት ወቅት ለወላጆች ቀለል ያሉ ምግቦችን (ዳቦ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎ፣ ብስኩት፣ ሻይ፣ ቡና…ወ.ዘ.ተ) ማቅረብ ውይይቱን ይበልጥ ወዳጃዊ መንፈስ እንዲኖረው ይረዳል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ በቀጥታ በሕፃናት የደህንነት ስሜት ላይ አውንታዊ ድርሻ አለው፡፡ ለምሳሌ በውይይቱ ወቅት የልጆች አስተዳደግን በተመለከተ የአባቶች ሚና ምን መሆን አለበት? የሚል ርዕስ የመወያያ ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንዳንድ ባሕሎች የሕፃናት ጉዳይ ሁሉ የእናቶች ኃላፊነት ነው ተብሎ ስለሚታመን አባቶች ከአፀደ-ሕፃናት የራቁ ናቸው፡፡ በሌሎች ባሕሎች ደግሞ እናቶች በቤት ውስጥ ስራ የተወሰኑ በመሆናቸው ሕፃናትን አጅበው ወደ አፀደ-ሕፃናት የሚሄዱ አባቶች ብቻ ናቸው፡፡ ስለሆነም እንደ አካባቢው ባህል አባቶችን ወይም እናቶችን በተናጠል የሚያስተናግዱ መድረኮች ማዘጋጀት መልካም ነው፡፡ እነዚህ የውይይት መድረኮች ወላጆች እንደየፍላጎታቸውና ችሎታቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን፣ መጫወቻዎችን፣ አሻንጉሊቶችን በመስራትና በመጠገን እንዲሁም ለሕፃናት የሚሆኑ የተለያዩ መጽሐፍትን በመለገስ ለት/ቤቱ ጠቃሚ አገልግሎት የሚሰጡባቸው መድረኮች ናቸው (ለምሳሌ የጨርቅ ወይም የሹራብ ኳሶች፣ የቁርጥራጭ ጨርቅና ሌሎች አሻንጉሊቶች፣ ቦርሳዎች፣ ተፍቀው የተሠሩ የእንስሳት ምስሎች ወይም ቅርጾች፣ የፎጣ መስቀያዎች…ወዘተ)፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የውይይት መድረኮች ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያጫወቷቸውን ጨዋታዎች የሚማሩባቸው መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ከወለጆች የሚሰበሰቡት የአሻንጉሊቶችና የመጽሐፍት ብዛት እየጨመረ ሲመጣ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ወላጆች በማዋስ ልጆቻቸውን በቤታቸው ውስጥ እንዲረዱ የሚያስችል ቤተ-መጽሐፍት ማደራጀት እንችላለን፡፡ በአፀደ-ሕፃናት ውስጥ  ወላጅ ከልጁ ጋር በአንድ ተግባር እንዲሳተፍ የሚያስችል ክፍለ-ጊዜ መመደብ የወላጅና-ልጅ ግንኙነትን ከማጠናከሩም ባሻገር የአፀደ-ሕፃናታችንን ውበት ይጨምራል፡፡ ሆኖም ከወላጆች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች የትልቅ ቡድን ስብሰባዎች ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡ ከአንድ ወይም ሁለት ወላጆችም ጋር ስብሰባዎች ሊያዘጋጁ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ምን እንደሚያስቡና ወደፊት ምን እንዲሆኑላቸው እንደሚፈልጉ ለማወቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በትምህርት ዓመቱ ከወላጆች ጋር የመሰረትናቸውን ግንኙነቶች አጠናክረን መቀጠሉ አማራጭ የለውም፡፡ ከወላጆች ጋር በዓመቱ መጨረሻ አንድና ረዥም ስብሰባ ከማካሄድ በርካታ አጫጭር ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት ይመረጣል፡፡ በተጨማሪም ከወላጆች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በደብዳቤዎች፣ መጽሄቶች፣ ጋዜጦችና በስልክ ጥሪዎች አማካኝነት አጠናክረን መቀጠሉ ለወደፈት ግንኙነታችን ጠቃሚ ነው፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ለማድረስ ጠዋት፣ ጠዋት ወደ አፀደ-ሕፃናታችን በሚመጡበት ወቅት ከእነርሱጋር ከምንለዋወጣቸው አንድና ሁለት ቃላት ውስጥ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡ በተጨማሪ በአፀደ-ሕፃናታችን የመግቢያ በር ላይ ለወላጆች ብቻ የሚያገለግል የአስተያየት መስጫ ኤንቨሎፕ ወይም መዝገብ ካዘጋጀን ከወላጆች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ይበልጥ ይጠናከራል፡፡ ወላጆች ከሚያደርጉት የአፀደ-ሕፃናታችን ጉብኝት በተጨማሪ እኛ መምህራንም በዕቅድ ላይ ተመስርተን የሕፃናትን መኖሪያ ቤቶች የመጎብኘት ተነሳሽነት ቢኖረን መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን የመኖሪያ ቤት ጉብኝት ለማድረግ ተስማሚ ወቅቶችን መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕፃን በሚታመምበት ወቅት መጎብኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ወላጆች ስለ ልጆቻቸው የጽሑፍ መረጃዎችን እንዲይዙ እንፈልግ ይሆናል፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን ተከታትለው መረጃ እንዲሰበስቡ የሚያስችሏቸው መሪ ጥያቄዎችን አዘጋጅተን እንስጣቸው፡፡ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ወላጆች ከሆኑ ለጥያቄዎቹ የተሰጡትን መልሶች በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ መዝግበው እንዲይዙ በአክብሮት እንጠይቃቸው፡፡ ሊቀርቡ የሚችሉ ጥቂት ጥያቄዎች የሚከተሉትን ሊመስሉ ይችላሉ - ልጅዎ ከሌሎች ሕፃናት ጋር ይቀላቀላል? ይተባበራል? በምን ዓይነት ሁኔታ ይተባበራል? የጋራ ጨዋታ ለመጫዎት ከጓደኞቹ መካከል ማንን ይመርጣል? መሳተፍ የሚፈልጋቸው ተግባራት የትኞቹ ናቸው? ለምን ያህል ጊዜ መሳተፍ ይፈልጋል? ለብቻው መጫዎት የሚፈልገው የጨዋታ ዓይነት ምንድን ነው? ተግባራትን ይፈጥራል? ወይስ በሚሰነዘሩ ሀሳቦች ላይ ያተኩራል? ሌሎች ሰዎች የሚሉትን ለማድመጥ ፈቃደኛ ነው? ከሰዎች ጋር ያለው ማህበራዊ ግንኙነት ምን ይመስላል? ገደቦችን ይቀበላል? ይስማማል? ስሜቶችንስ እንዴት ያስተናግዳል? ስለራሱ ያለው ስሜት ምን ይመስላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት የምንሰበስባቸው መረጃዎች ሕፃናት በት/ቤት ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው እንዲውሉ ከሚያስችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም በሕፃናት ደህንነትና እንክብካቤ አስፈላጊነት ላይ ተጨማሪ መሠረታዊ ነጥቦችን በቀጣይ መልዕክቴ ይዤ እስከምቀርብ ድረስ ሁላችንም በያለንበት ቸር ይግጠመን እያለኩ ለዛሬ እሰናበታለሁ፡፡

መልካም መልካሙን ለሕፃናት!!!

መምህር ሣህሉ ባዬ

 (MA in Chid Development, BA in Pshychology,

MBA & IDPM in Project Management)

Email: sahilubaye@gmail.com and/or ecd@ethionet.et

                                                            www.enrichmentcenters.org


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”