call us now

251 1 911 23 08 57 / 60 76 06

How Brain Archtecture Develops?

መልዕክተ - ትምህርት 14

የጨቅላ ሕፃናት ስረዓተ-ነርቭ ዑደትና የአንጎል ውቅር፡-

   በዛሬዋ ትምህርታዊ መልዕክት የጨቅላ ሕፃናት ስረዓተ-ነርቭ ዑደትና የአንጎል ውቅርን በተመለከተ የዘመናችን የስርዓተ-ነርቭ ስነህይወት ሣይንስ (ኒዮሮባዮሎጂ) ባለሙያዎች በጥናታቸው የደረሱባቸውን ስርነቀል አዳዲስ ግኝቶችና የጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ቁርኝትን እንዳስሳለን፡፡

   አንድ ውጤታማ ወይም ስኬታማ ማህበረሰብ የሚመነጨው ከጤናማ የጨቅላ ሕፃን የእድገት ሂደት ነው፡፡ ጤናማ የሆኑ ዜጎችንና ጠንካራ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚስችሉ መሰረታዊ ስራዎች የሚሰሩት በጨቅላ ሕፃንነት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ በመሆኑም ዋናውና መሰረታዊ ነጥብ እነዚህን ለህብረተሰብ እድገትና ህልውና ወሳኝ የሆኑ ስራዎች በጨቅላ ዕድሜ ክልል እንዴት እንስራቸው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ምሁራን የሚከተሉትን ምክሮች ለግሰዋል፡፡

  በጨቅላ ሕፃነት ዘመን ከአካባቢ ጋር የሚደረጉ ግንኝነቶችና የሚቀሰሙ ልምዶች ለሕፃናት ስርዓተ - ነረቭ ዑደት፣ ለአንጎል አወቃቀርና እድገት ወሳኝ ኩነቶች ናቸው፡፡ በወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ ሞግዚቶች፣ ሕፃናት ተንከባካቢዎች እና በሕፃናት መካከል ሰጥቶ - የመቀበል ምቹ መደላድል ሲኖር አስደናቂ የአንጎል ውቅር ይፈጠራል፡፡ የስነህይወት ተመራማሪዎች እንደሚያስረዱን የጨቅላ ሕፃን አንጎል የተረጋጋና ከአካባቢው ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ አካል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሌለበት ግን አስቸጋሪ ነገሮች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በጨቅላ ሕፃንነት ዕድሜ አንጎል የሚያከናውናቸው ተግባራት በቅደም ተከተል ተፈትሸዋል፡፡ እነርሱም ግንዛቤ፣ ቋንቋ፣ ማህበራዊና የስሜት ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት በሚደንቅ ሁኔታ አንዱ ከሌላው የተጋመዱና ውብ ሆነው የተሳሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ትስስሮች አንጎል የማይለያያቸው ስለሆነ የእኛ ተግባር የአንጎልን ጤናማና ሁለንተናዊ እድገት ሂደት በምቹ መሰረት ላይ ማስጀመር ነው፡፡ የግንዛቤና ቋንቋ እድገትን ከማህበራዊና ስሜታዊ እድገት ለይተን ልናይ ስለማንችል አንዱን ከሌላው አስተሳስረን ማየትና በዚህ ዕድሜ አንጎል ተለጣጭና በቃለሉ ቅርፅ የማውጣት ባህሪይ ያለው አካል መሆኑን መረዳት ነው፡፡

   የስርዓተ - ነርቭ ስነህይወትና የአእምሮ እድገት መሰረታዊ ጠባይ እንደ ፕላስቲክ በቀላሉ ቅርፅ መያዙ ወይም መለጠጡ ሲሆን ይህም ጠባይ “ፕላስቲሲቲ (Plasticity)” በመባል ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ አንጎል የፕላስቲክ ጠባይ አለው ሲባል ምን ማለት ነው? “ፕላስቲሲቲ” አንጎል ከአካባቢው ጋር የሚኖረውን የመስማማት ወይም “የመደመር” ችሎታና በዕድገትና ብስለት ሂደት ውስጥ የሚያሳየውን ተለዋዋጭ ጠባይ ያመለክታል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ከፍተኛ የአንጎል “ፕላስቲሲቲ” የሚከሰተውና ከፍተኛ የመስማማትና ቅርፅ የመያዝ ዕድል የሚፈጠረው በጨቅላ የሕፃንነት የዕድሜ ክልል መሆኑን ምሁራን አስምረውበታል፡፡ በዚህ ወቅት መልካም ዘር ካልዘራን ዕድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር የአንጎል “ፕላስቲሲቲ” ጠባይ እየቀነሰና እየደከመ ስለሚሄድ አንጎልን ለማረቅ ወይም ለመቅረፅ ብሎም ጤናማ ሰብዕና ለመገንባት አዳጋች እየሆነ ይመጣል፡፡ ሁኔታውም “በዕድሜ የገፋ እንስሳን አዲስ ዘዴ ወይም ብልሃት አያስተምሩም” እንደሚባለው አባባል ይሆናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ስለ ሕፃናት እድገት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ስናስብ ስለ ጨቅላ ሕፃናት አንጎል ውቅርና እድገት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ፍሬው ያማረ ዘር ለማግኜት አካባቢያዊ ምቹ መደላድል በመፍጠር ተገቢ ስራ በትክክለኛው ወቅት ማከናወን እንደሚገባን ያስገነዝበናል፡፡ ስለሆነም በትክክለኛው ወቅት ተገቢ ስራ መስራት ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ቆጣቢና አማራጭም፣ አቋራጭም የለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እነጂ የነርቭ ስረዓተ-ዑደትና የአንጎል ወቅር እየበሰለ ሲሄድ ለማሻሻል ወይም ለመለወጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ዕድሉ ፈፅሞ የተዘጋ አይደለም፡፡

       በጨቅላነት ወይም በድክ፣ ድክ ዕድሜ የሰው ልጅ አንጎል በሴኮንድ 700 የስርዓተ - ነርቭ ግንኝነቶች የሚያከናውን ሲሆን እየበሰለ ሲሄድ በርካታ ትሪሊዮን (Trillions) ግንኝነቶች ያከናውናል፡፡ ስለ አንጎል ረቂቅ አፈጣጠር ሳስብ አንድ የስራ ባልደረባዬ “አእምሯችን የማናውቀው ፕላኔት ነው ይባላል” የሚለውን አባባሉን ያስታውሰኛል፡፡ የስርዓተ - ነርቭ ዑደቶች የጊዜ ሰሌዳ ተፈጥሯዊ ወይም ጀነቲካዊ ነው። ግንኙነታቸውም በአካባቢያዊ ተፅዕኖ ይወሰናል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት በሚስተዋሉ የስርዓተ - ነርቭ ዑደቶች ማየትና መስማት ቀዳሚ የስሜት ክስተቶች ሆነው ይከሰታሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኃላ ደግሞ ቋንቋን የመጠቀም፣ ድምፆችን የመለየት፣ ቀላትንና ድምፆችን የማመሳሰል ችሎታዎች ይስተዋላሉ፡፡ ጨቅላ ሕፃናት እንደተወለዱ ለሰው ልጅ መግባቢያ የሆኑ ቋንቋዎችን ሁሉ የመማር፣ የማወቅና የመጠቀም ተፈጥሯዊ ፀጋ አላቸው፡፡ በመጨረሻም ከፍተኛ የአእምሮ ተግባራት በመሆናቸው ምክንያት ከሁሉ ዘግይተው የሚዳብሩት የመገንዘብ፣ ችግሮችን የመፍታትና መሰናክሎችን የማለፍ ችሎታዎች ናቸው፡፡

     በአጠቃላይ ለጨቅላ ሕፃናት ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ይህን ወሳኝ ወቅት (Sensitive period) በተረጋጋ መሰረት ላይ መጀመር በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነ ቤተሰቦች፣ ት/ቤቶች፣ ህብረተሰበና ለሕፃናት ጤናማ እድገት የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አንኴር ጉዳይ  መሆኑን እየጠቆምኩ የዕለቱ መልዕክቴን እቋጫለሁ፡፡ ቸር ይግጠመን!!

መልካም፣ መልካሙን ለሕፃናት!!

ሣህሉ ባዬ ዓለሙ

የፕሮጄክት ማኔጅመንት፣ የሕፃናት ዕድገትና ስነልቦና ባለሙያ

www.enrichmentcenters.org

 

 


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”