call us now

251 1 911 23 08 57 / 60 76 06

Early Child Development

መልዕክተ - ትምህርት 13

የሕፃናት ጤናማ ዕድገት መሰናክሎችና መፍትሄዎች:-

  አዳዲስ ሣይንሳዊ ግምቶቸ እንደሚጠቁሙት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላችው አገራት ውስጥ የሚኖሩና ዕደሜያቸው ከአምስት ዓምት በታች የሆኑ 250 ሚሊዮን (43%) ሕፃናት በድህነትና ቅንጨራ ምክንያቶች ክሂሎታቸውን መጠቀም የተሳናችው ናቸው። ይህን ችግር አስመልክቶ Maureen M Black, Susan P Walker, Lia C H Fernald, Christopher T Andersen እና ጓደኞቻቸው እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም “Advancing Early Childhood Development: from Science to Scale 1” በሚል ርዕስ በጋራ ባሳተሙትና “ላንሰንት” ለተባለ የሕፃናት እድገትን ለሚያጠና ኮሚቴ ባቀረቡት የጥናት ሰነዳችው ላይ እንድገለፁት በእርግዝና ወቅትና ከውልደት በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት የእድገት ዓመታት የሚከሰቱ ችግሮች በሕፃናት አዕምሯዊ ዕድገት፣ በልጆችና በአሳዳጊዎች መካከል በሚፈጠር ቤተሰባዊ ፍቅርና በቅድመ መደበኛ ትምህርት የመከታተል አቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንዲከሰት ምክንያቶች ናቸው ይላሉ። በወቅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ችግሩን መከላከል ካልተቻለ ተባብሶ እንደሚቀጥል በዚሁ ጥናት ተጠቁሟል።

     ከስሃራ በታች ባሉ ሃገራት የሚኖሩ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑና በድህነትና ቅንጨራ ችግሮች ሳቢያ ክሂሎታቸውን መጠቀም ያልቻሉ ሕፃናት ብዛት እንደሚከተልው ተዘርዝሯል። በጃንዋሪ 7, 2017 በ www.thelancet.com Vol 389 የላንሴት ድረገፅ ላይ የታተምው መረጃ እንደሚያስረዳው እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ብዛት በ2004 ዓ.ም 124,900,000፣ በ2010 ዓ.ም 143,300,000፣ የቀነጨሩ ሕፃናት በዛት በ2004 ዓ.ም 53,900,000፣ በ2010 ዓ.ም 55,100,000፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናት ብዛት በ2004 ዓ.ም 67,500,000፣ በ2010 ዓ.ም 72,300,000 ሲሆን በአጠቃላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑና ክሂሎታቸውን መጠቀም የተሳናቸው ሕፃናት ብዛት በ2004 ዓ.ም 87,600,000፣ በ2010 ዓ.ም ደግሞ 94,800,000 ሕፃናት እንደነበሩ ታውቋል።

   በማህበራዊ ስነ-ምህዳር (Social Ecology) ውስጥ ያለው የሕፃናት ስርዓተ-አስተዳደግ ሞዴል ሁለት ገፅታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ማህበራዊ ሲሆን ሁለተኛው መዋቅራዊ ነው፡፡  ማህበራዊ ተሳትፎ ጤናማ አካባቢ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ሰብዓዊ ሃብት፣ የእናቶች መማር፣ የወላጆችና አሳዳጊዎች አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትን … ወ.ዘ.ተ ያካትታል፡፡ መዋቅራዊ ተሳትፎ ደግሞ ፖለቲካ፣ ፖሊሲዎች፣ ሕግጋት፣ ድጋፍ ሰጪ ስርዓት፣ ደንቦች፣ አሰራሮችንና የኢኮኖሚ ዋስትናን በአንድ ጎን ግጭቶች፣ ጦርነቶች፣ ድርቅ፣ ርሃብንና የባህል ልዩነቶችን በሌላ ጎን ያካትታል፡፡ እነዚህ አዎነታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች በሕፃናት እድገት ላይ የሚኖራቸው ሚና ሊታረቅ የሚችለው በጤናማ የአስተዳደግ ስርዓት ሲታገዝ ብቻ ነው፡፡ 

   ስለሆነም የሕፃናትን ክሂሎት፣ የፈጠራ ችሎታና ጤንነታቸውን ለመታደግ በርካታ ሴክተሮችን በማሳትፍ ለጤና ጥብቃ፣ ፍቅር ሰጥቶ በመቀበል ላይ ለተመሰረተ ጤናማ የአስተዳደግ ስርዓት ቅድሚያ መስጠትና እንደሚከተለው ለተዘረዘሩት 5 መርሆች ትኩረት መሰጠት ተገቢ ይሆናል፡፡

1ኛ.  ጤና፡- በሽታን መከላከል፣ ህክምና፣ ክትባት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፅዳት….፣

2ኛ.  ምግብ፡- የተመጣጠነ ምግብ፣ ተጨማሪ ምግብና የእናት ጡት….፣

3ኛ. ሰላምና ደህንነት፡- ቤተሰቦቻቸውን በሞት አጥተው በከፋ ድህነት ለሚኖሩ ሕፃናት ከማሳደጊያ ተቋማት ውጪ ያሉ ቤተሰባዊ የድጋፍ አማራጮችን ማመቻቸት፣

4ኛ. መልስ ሰጪ እንክብካቤ፡- በሂደት ለሚከሰቱ ችግሮች መልስ በመስጠት የሕፃናትን ስሜት መደገፍና    

5ኛ. ቅድመ መደበኛ ትምህርት፡- ጥራት ያለው የቅድመ መደበኛ ትምህርት መስጠት። በተጨማሪም በት/ቤቶችና በምኖሪያ ቤቶች ውሰጥ አጋዥ መጽሐፍት፣ አሻንጉሊቶች፣ መጫዎቻ ቁሳቁሶች… ወ.ዘ.ተ ማመቻቸት ዋና፣ ዋና መርሆች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ጤናማ የሕፃናት እድገት ሊፈጠር የሚችለው በሕፃናትና በወላጆች (አሳዳጊዎች) የሁለትዮሽ መልካም ግንኙነት ላይ መሆኑን በቅድሚያ መረዳት ተገቢ ነው፡፡  በጤናማ እንክብካቤ ስርዓት፣ በሕፃናት ጤንነት፣ አካላዊ እድገትና ሰብዓዊ ልማት መካከል ጥብቅ ቁርኝት ያለ መሆኑን ምሁራን አስምረውበታል፡፡ ስለሆነም ማህበራዊና መዋቅራዊ ተሳትፎዎችን ፈትሾ ለመጠቀም ዓለም አቀፋዊ፣ አገራዊ፣ ክልላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ማፈላለግ ጠቃሚ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ የዕለቱ መልዕክቴ ነው። በያለንበት ቸር ይግጠመን!

መልካም፣ መልካሙን ለሕፃናት!!

ሣህሉ ባዬ ዓለሙ

የፕሮጄክት ማኔጅመንት፣ የሕፃናት ዕድገትና ስነልቦና ባለሙያ

www.enrichmentcenters.org


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”