call us now

251 1 911 23 08 57 / 60 76 06

Child Development Part Four

 

ነገ ሩቅ ነውን?

የነገውን ሰው ማነጽ - ይድረስ ለወላጆችና መምህራን  (ክፍል 4)

     የተከበራችሁ አንባቢያን! ያሳለፍነው ሳምንት የሰላም ሳምንት ሆኖ እንዳለፈላችሁ ተስፋ በማድረግ በዛሬዋ መጣጥፌ ለማቅረብ ቃል ወደገባሁት ርዕሰ ጉዳይ እሸጋገራለሁ፡፡ መኖሪያ ቤታችንና አፀደ-ሕፃናታችን የትም ይሁን የት፣ መጠናቸውና ስፋታቸው ምንም ይሁን ምን በሕፃናት አስተዳደግ ሂደት ተገቢ ትኩረት የሚሹ መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ በመሆኑም የሕፃናት ደህንነትና ጥበቃ አስፈላጊነት ላይ ተጨማሪ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የሕፃናት ደህንነትና ጥበቃ ማለት የሕፃናት መሠረታዊ ፍላጐት ማለት ነው!!

     መኖሪያ ቤቶችና ት/ቤቶች ለሕፃናት ምቾት፣ ደስታና እርካታ የሚሰጡ ተቋማት መሆን አለባቸው፡፡ በግድግዳዎች ላይ የተንጠለጠሉ ዕቃዎች ስለ ሕፃናት የሚናገሩ ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ ሁሉም ነገሮች ለሕፃኑ ዕይታ አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ መንጠልጠል ይኖርባቸዋል፡፡ የዛጉ ቁርጥራጭ ብረቶችንና ሹል ጫፎች ያሏቸውን ነገሮች ከመጠቀም መታቀብ ጠቃሚ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤቶችና መማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ያፈነገጡ ሚስማሮች፣ ሹልና ስለታም ዕቃዎች በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ገመዶችን በጥንቃቄ መዘርጋትና ከመተላለፊያ መንገዶች ላይ ራቅ አድርጎ ማስቀመጥ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ወለሎችና ግድግዳዎች ከአፈር፣ ከሸክላ፣ ከእንጨት፣ ከብረት፣ ከአሸዋና ሲሚንቶ ድብልቅ ወይም ከድንጋይ የተሠሩ ቢሆኑም ለማፅዳትና ለመንከባከብ ምቹና ለግቢው ተስማሚ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ወለላችን ከጣውላ የተሠራ ከሆነ ሹል፣ ስንጣሪና ስባሪ ነገሮች እንዳይገኙ በብርጭቆ ወረቀት ጥሩ ሆኖ መታሸቱን እናረጋግጥ፡፡ ነገር ግን ወለሉ በጣም ከመቦረሹ የተነሳ አንሸራታች ወይም የሚያዳልጥ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ግድግዳዎችን በቀለም ቅብ ሥዕሎች ማስዋብ ከፈለግን ቀላል፣ ለስላሳና የማያንፀባርቁ ቀለሞችን እንጠቀም፡፡ ይሁን እንጂ የምንጠቀምበት ቀለም በውስጡ የብረት ቀለም ሊኖረው አይገባም፡፡ መሠረታቸው ብረት ቀለም የሆኑ ቀለማት ለሕፃናት አደገኛ ስለሆኑ እንደነዚህ ዓይነት ቀለማትን ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ በወለል ላይ የሚነጠፉ ሰሌኖችና ምንጣፎችም ድምፅን መከላከል ይችላሉ፡፡ ጤንነታቸው የተጠበቀላቸው ሕፃናት ንቁና ቀልጣፋ ናቸው፡፡ ጡንቻቸውንም ለማዳበር የሚረዳቸው በነፃነት የሚያንቀሳቅሱበት ምቹ ስፍራ ልናዘጋጅላቸው ይገባል፡፡

    ሕፃናት ዕውቀት እንዲያዳብሩ በመኖሪያ ቤቶችና ት/ቤቶች ውስጥ ስንረዳቸው የምንጠቀምባቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች በክብደት ቀለል ያሉ፣ በአገልግሎታቸው ሁለገብና ምቾት የሚፈጥሩላቸው ሆነው መዘጋጀት አለባቸው፡፡ አንድን ዕቃ ለአንድ ተግባር ብቻ ከመጠቀም ለበርካታ ተግባራት መጠቀም ተመራጭ ነው፡፡ እነዚህ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች በቀላሉ የሚታጠፉ፣ የሚዘረጉ፣ የሚለመጡ፣ እንደሁኔታው የሚለዋወጡ፣ ጠንካራ፣ ለግልና ለቡድን ተግባራት የሚያገለግሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ አሠራራቸውን በተመለከተ በአካባቢያችን የሚገኙ ነገሮችን በማፈላለግ ችግር ቻይ እንዲሆኑ በማድረግ በርከት አድርጎ መሥራት ይቻላል፡፡ በጣም በርካታ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በአካባቢየችን ከተጣሉ ወይም ከተወገዱ ነገሮች መሥራት እንችላለን፡፡ ዋናው ነጥብ በአካባቢያችን የሚገኙ ነገሮችን ፈትሸንና ችሎታችን ተጠቅመን ለትምህርታዊ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ መቻላችን ነው፡፡ ስለ ትምህርት መርጃ መሳሪያ አዘገጃጀት እራሳችንን እንጠይቅ፡፡ “ከነዚህ ነገሮች ምን መስራት እችላለሁ? ሕፃናትን በመርዳት ሂደት ውስጥ እንዴትስ ልጠቀምባቸው? እንዴትስ ለዓላማዬ ማስፈፀሚያ ያገልግሉኝ?” ከእነዚህ ነገሮች ልጄ ምን ትምህርት መቅሰም ይችላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን አንስተን እራሳችንን እንጠይቅ፡፡ አንዳንዴ የተቃርኖ ትምህርታዊ አቀራረብ ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ቤታችንና ት/ቤታችን በጩኸታማ ኢንዱስትሪያዊ አካባቢ የሚገኙ ከሆነ ክፍሎችና ኮርኒሶችን ድምፅ በማያስተላልፉ ማቴሪያሎች መሸፈን ተገቢ ነው፡፡ አንድ ወጪ የማይጠይቅ ጠቃሚና ቀላል ዘዴ የዕንቁላል መያዣ ካርቶኖችን በማፈላለግ ኮርኒስ እንዲሆኑ መጠቀም ነው፡፡ የዕንቁላል ካርቶኖችን ውብ አድርጐ በመቀባት ማስዋብ ይቻላል፡፡ ይህ ዘዴ የአየሩ ጠባይ አስቸጋሪ በሆነባቸውና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ተባዮች ወይም ጎጂ ነፍሳት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ሁሉ አገልግሎት መስጠት ይችላል፡፡

     የመጀመሪያዎቹ የዕድገት ዓመታት ሕፃናት አዳዲስ ነገሮችን የሚማሩባቸው፤ ኬሌሎች የዕድገት ደረጃዎች በተለየ አዕምሮ ፈጣን እድገት የሚያሳይበት፣ ስለራሳቸውና ማንነታቸው ግንዛቤ ማግኘት የሚጀምሩበት ዓመታት ናቸው፡፡ ስለሆነም እኛ ወላጆችና መምህራን በዚህ የእድገት ሂደት ውስጥ የሚገኙትን ሕፃናት እያጫወትን በማስተማር የነገውን ሰው ደህንነት መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እዚህ ላይ ጥቂት ምሳሌዎችን በማንሳት ሀሳቡን ማጠናከር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እያንዳንዱ ሕፃን የግል የሆኑ ንብረቶቹን ማለትም የሰራቸውን ስዕሎች፣ የሰበሰባቸውን ላባዎች፣ ጠጠሮች…ወዘተ የሚያስቀምጥበት ስፍራ ወይም ከረጢት ወይም ሳጥን በግል እንዲኖረው በማድረግና የሕፃኑን ስም ብቻ የያዘ ውስን ቦታ በማዘጋጀት የተፈላጊነት ስሜቱን ማዳበር ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በሕፃናት ቁመት ልክ የተዘጋጀና ምስል የሚያሳይ መስታዎት በእጅ መታጠቢያ ሥፍራ አካባቢ ማስቀመጥ ሕፃናት አቋማቸውን እንዲያስተውሉ፣ ለንፅህናና ውበት ትኩረት እንዲሰጡ ያበረታታቸዋል፡፡ በተጨማሪ ሕፃናት ሲያርፉ ወይም ሲተኙ ደህንነታቸው የተጠበቀ ሁኔታ የተፈጠረላቸው መሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሕፃናት በዕረፍት ጊዜ ተሸፋፍኖ መተኛት ስለሚያስደስታቸው አልባሳት ቢዘጋጅላቸው መልካም ነው፡፡ በመማሪያ ከፍል ውስጥ ዕቃዎችን በማነሳሳት ሕፃናት ሰፊና በቂ ዕረፍት ማድረጊያ ስፍራ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የዕንቅልፍ ወይም የሸለብታ ስፍራ ፀጥታው የተጠበቀ፣ ንፁህና ምቹ እንዲሆን ሁኔታዎችን እናመቻችላቸው፡፡ ሕፃናት ለመተኛት ፈቃደኛ ካልሆኑ እንዲተኙ ማስገደድ ተገቢ አይሆንም፡፡ የተረበሸው ስሜታቸው እስኪረጋጋ ከአጠገባቸው ሳንለይ ድጋፍ እንስጣቸው፣ ተረቶች፣ አጫጭር ታሪኮች፣ ሙዚቃዎችና መዝሙሮች፣ እንዲያዳምጡ ሁኔታዎችን እናመቻችላቸው፡፡ ሕፃናት በቤት ውስጥ ከሚወዱት አሻንጉሊት ወይም መጫወቻ ጋር የመተኛት ልምድ ካላቸው በአፀደ-ሕፃናትም ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታን ማመቻቸት ጠቃሚ ነው፡፡ ወደ መፀዳጃ ክፍል ለመሄድ ሲፈልጉና ድንገተኛ ሁኔታ ሲከሰት በፍጥነት አካባቢውን ለቀው መሄድ የሚያስችቸው ሁኔታ ማመቻቸት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህንና መሰል ተግባራትን በማከናወንና እራሳችንን በሕፃናት ጫማወች ውስጥ አስቀምጠን ውስጣዊ ስሜታቸውን በማንበብ ደህንነታቸውንና ምቾታቸውን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ሕፃናት ለዛ ያላቸው ቀልዶችና ጨዋታዎች ይወዳሉ፤ ይደሰታሉም፡፡ ጥሩ አድማጭ ከሆንላቸውም ደግሞ አስደሳች ቀልዶቻቸውን ያካፍሉናል፡፡ በተራቸው ሕፃናት ጥሩ አድማጭ በመሆን የእኛን ጨዋታበመጋራት አድናቂዎች ይሆናሉ፡፡ ማንም ሰው እንዲሳቅበት ባይፈልግም ሕፃናት ከእኛ ጋር ሲሆኑ መሳቅ ያስደስታቸዋል፡፡ ስለዚህ ቀደምን ዝግጅት ብናደርግ መልካም ነው፡፡ ወላጆችና መምህራን አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነታችን የተጠበቀ ከሆነ ሕፃናት መንፈሳዊ መረጋጋት ያገኛሉ፡፡ ሰላምና ደህንነታቸው የተጠበቀና ጤናማ ሰብዕና ያላቸው ሆነው ያድጋሉ፡፡ ይህም ሁኔታ በወደፊት ህይዎታቸው ላይ ጠቃሚ ተፅዕኖ ያለው ለመሆኑ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ሕፃናት በተለያዩ ጨዋታዎች አማካኝነት በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን መማርና ጤናማ ሰብዕናቸውን መገንባት እንደሚችሉ የመስኩ ተመራማሪዎች በተለያዩ ጊዚያት አብስረዋል፡፡ በመሆኑም በተከታዩ ጽሁፌ የምንመለከተው ነጥብ ጨዋታ በሕፃናት ሁለንተናዊ የሰብዕና እድገት ላይ ስላለው አይተኬ ጠቀሜታ ይሆናል፡፡ እስከዚያው በያለንበት ቸር ይግጠመን እያልኩ ለዛሬ በዚሁ እሰናበታለሁ፡፡

መልካም መልካሙን ለሕፃናት!!!

መምህር ሣህሉ ባዬ

 (MA in Chid Development, BA in Pshychology,

MBA & IDPM in Project Management)

Email: sahilubaye@gmail.com and/or ecd@ethionet.et

                                                            www.enrichmentcenters.org

 


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”